የፌደራል መንግሥት በተቆጣጠራቸው ከተሞችና አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች ወደ ዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው መመለስ ጀምረዋል... ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ - ኢዜአ አማርኛ
የፌደራል መንግሥት በተቆጣጠራቸው ከተሞችና አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች ወደ ዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው መመለስ ጀምረዋል... ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2013(ኢዜአ) በትግራይ ክልል የፌደራል መንግሥት በተቆጣጠራቸው ከተሞችና አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች፣ በጸጥታ ኃይሎች ጥበቃ እየተደረገላቸው ወደ ዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው መመለስ መጀመራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አስታወቁ።
ሕግ በማስከበር ተልዕኮው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ባለፉት ጥቂት ቀናት ያስመዘገበው ድል የሚደነቅ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስቡክ ገጻቸው እንዳሰፈሩት ሠራዊቱ ትናንት ምሽት በአዲግራት ዙሪያ ያሉትን አካባቢዎች ከተቆጣጠረ በኋላ፣ ዛሬ ደግሞ አዲግራትን ከሕወሓት ኃይል ሙሉ በሙሉ ነፃ አውጥቷል ነው ያሉት።
ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን፣ ለዜጎች ሰብአዊና ማኅበራዊ ፍላጎቶች የሚሟሉበትን መንገድ እናመቻቻለንም ነው ያሉት።
የሰብአዊ ድጋፍ ክንውኖችን ለመከታተል በፌደራል መንግሥት የተዋቀረው ከፍተኛ ኮሚቴ፣ ተመጣጣኝ እና ወቅታዊ ድጋፍ ለማቅረብ የሚያስችል መረጃን እንዲያሰባስቡ ተጨባጭ ሁኔታውን የሚያጣሩ ልዑካንን ወደ ስፍራው መላኩንም አስታውቀዋል።
በተጨማሪም፣ ኮሚቴው ባለፉት ቀናት መኖሪያቸውን ጥለው የተሰደዱትን ዜጎች ሁሉ ወደ ቀያቸው ለመመለስ እና ለማቋቋም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መሥራቱን ይቀጥላል ብለዋል።
የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ አጠቃላይ ደኅንነት እና ጤንነት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጥ ስለ ሆነ፣ በትግራይ ክልል መረጋጋት እንዲሰፍን እና ዜጎች ከጉዳት እና እጦት ነፃ እንዲሆኑ አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ገልጸዋል።