"የነገ አገር ተረካቢ ሕጻናትን መደገፍ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል '' .... ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
"የነገ አገር ተረካቢ ሕጻናትን መደገፍ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል '' .... ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2013(ኢዜአ) የነገ አገር ተረካቢ ሕጻናትን በስነ -ምግባር የታነጹ እና ብርቱ ዜጎች እንዲሆኑ በሁሉም መስክ መደገፍ እንደሚገባ የኢስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዓለም የህጻናት ቀንን ምክንያት በማድርግ በቀጨኔ የሴት ህጻናት ማቆያ ማዕከል በመገኘት ለህጻናቱ የምሳ ግብዣ አድርገዋል።
በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግርም "ዛሬ በህጻናት ላይ አስበን እና አቅደን ካልሰራን ጠንካራ ትውልድ መፍጠር አንችልም" ብለዋል።
ለህጻናት በሁሉም መስክ እገዛ በማድረግና በመደገፍ በስነ-ምግባር የታነጹና አገር ወዳድ ዜጎች እንዲሆኑ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በተለይ በማሳደጊያ ማዕከላት ያሉ የህጻናቱ መምህራንና በቅርበት የሚከታተሉ የሥራ ኃላፊዎች ለህጻናቱ አልባሳትና ምግብ ከማሟላት ውጭ ትውልድን በመቅረጽ ተግባር ላይ እንዲያተኩሩ አደራ ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የሴቶችና ህጻናት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሐዲስ ኪዱ እንዳሉት አስተዳደሩ በህጻናቱ እድገት እና የተሻሉ ተግባራት ላይ በትኩረት እየሰራ ነው።
የከተማ አስተዳደሩ በ140 ሚሊዮን ብር በጀት "ደስተኛ ህጻናት ለአዲስ አበባ" የሚል ፕሮጀክት በአሥሩም ክፍለ ከተሞች ማስጀመሩን አንስተዋል።
የቀጨኔ መድኃኔዓለም የሴት ህጻናት ማቆያ ማዕከል ኃላፊ ወይዘሮ ሀብታም ነጋሽ፣ መንግሥት ህጻናቶቹን እየደገፈ ያለበት ሁኔታ መልካም መሆኑን አንስተዋል።
ሆኖም ህጻናቱን በስነ-ምግባር አንጾ በማሳደጉ ረገድ የባለሙያ እጥረት እንዳለ ገልጸው፣ ተጨማሪ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
በቀጨኔ መድኃኔዓለም የሴቶች ህጻናት ማቆያ ማዕከል እድሜያቸው ከ8 እስከ 18 የሚሆኑ 183 ህጻናት ይገኛሉ።
የዓለም የህጻናት ቀን "ትውልድን እንቅረጽ አገርን እንገንባ" በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ቀጨኔ የሴት ህጻናት ማቆያ ማዕከል ተከብሯል።
የዓለም የህጻናት ቀን ዘንደሮ የሚከበረው በዓለም ለ31ኛ ጊዜ እነዲሁም በኢትዮጵያ ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ ነው።