ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን 8 የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2013(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጭ 8 የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ስምምነት ተፈራረመ።

የተቋሙ ሰራተኞች" ደማችን ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን" በሚል የደም ልገሳ አከናውነዋል፡፡

 ባለሥልጣኑ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነቱን የተፈራረመው 118 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸውን የመንገድ ፕሮጀክቶች ለመገንባት ነው።

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ በግንባታው ከ15 እስከ 50 ሜትር ስፋት ያላቸው የኮንክሪትና አስፋልት መንገዶች የሚገነቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ግንባታው በየካ ጣፎ፣ በደንጋራ፣ በኮየ ፈጨና በጨፌ አካባቢ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ስራንም ያካትታል።

የፕሮጀክቶቹ  ግንባታ ከ9 እስከ 19 ወራት ተከናውኖ የሚጠናቀቅ መሆኑም ታውቋል።

በግንባታ ሂደቱም ለ2 ሺህ በላይ ሰዎች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሏል።

የመንገዶቹ መገንባት በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ያለውን የትራፊክ ፍሰት ለማሳለጥ የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ዮናስ አያሌው የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በጊዜውና በጥራት ይጠናቀቃል ብለዋል።

በግንባታው 50 ኪሎ ሜትሩ አስፋልት ሲሆን 68 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትሩ ደግሞ በኮብልስቶን ንጣፍ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የባለስልጣኑ ሰራተኞች ”ደማችን ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን” በሚል መሪ ሃሳብ ለመከላከያ ሰራዊቱ ደም ለግሰዋል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ በመከላከያ ሰራዊት ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ሰራተኞቹ የደም ልገሳ ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታከለ ለሉና ለመከላከያ ሰራዊቱ አጋርነታችንን ለማሳየት ደማችንን ለግሰናል ብለዋል፡፡

በእለቱ ከ1 ሺህ በላይ የባለስልጣኑ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ደም ለግሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም