ጽንፈኛው የህወሀት ቡድን የፈጸመው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በአለም አቀፍ የጦር ወንጀለኝነት እንደሚያስጠይቅ ምሁራን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ጽንፈኛው የህወሀት ቡድን የፈጸመው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በአለም አቀፍ የጦር ወንጀለኝነት እንደሚያስጠይቅ ምሁራን ገለጹ
አርባምንጭ፣ ህዳር 11/2013 (ኢዜአ) ጽንፈኛው የህወሀት ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቅ መሆኑን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ከተሳተፉት መካከል የህግ ምሁሩ አቶ ደርሶልኝ የኔአባት እንዳሉት የህወሀት ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ ነው።
ቡድኑ በሀገሪቱ ህገ-መንግስት ያሉ መሠረታዊ የግልጸኝነትና የተጠያቂነት መርሆችን በመጣስ የሀገሪቱን ሀብት በመዝረፍ፣ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱን ተናግረዋል።
ይባስ ብሎ በአሁኑ ወቅት ህዝቡ ይጠቀምባቸው የነበሩ የመሰረተ ልማት ተቋማትን በማውደም ከፍተኛ ኪሳራ አድርሷል ያሉት ምሁሩ ይህ ድርጊቱ በሽብርተኝነት ሊያስፈርጀው እንደሚችል ገልጸዋል።
በተጨማሪም ህፃናትን ለውጊያ መማገድን ጨምሮ ህወሀት በኢትዮጵያ በፈጸማቸው ህገ-ወጥ ድርጊቶች ከዓለም አቀፍ የጀኔቫ ስምምነት አንፃር በጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቅ እንደሆነ አስታውቀዋል።
በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት ተከትሎ መንግስት እያካሄደ ያለው ህግ የማስከበር ተግባር በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ተቀባይነት ያለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
መንግስት ሀገሩንና ህገ-መንግስቱን ከማንኛውም ኃይል ጥቃት የመከላከል ግደታ እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የታሪክ ምሁር የሆኑት አቶ ጣሰው ጡሚሶ ናቸው።
መከላከያ ሠራዊቱ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ወገንተኝነት ነፃ በመሆን ሀገሪቱ በውጭ ኃይል እንዳትደፈርና ሉዓላዊነቷን በማስከበር ተልዕኮውን ሲወጣ መቆየቱን ጠቁመዋል።
"ዘመናዊ የአስተዳደር ስርዓት ለማረጋገጥ ከመጣር ይልቅ የፖለቲካ ስልጣን በመቆናጠጥ የህዝብን ሀብት በመቀራመትና በህዝብ መካከል መከፋፈልና ሽብር በመፍጠር ህወሀት የታሪክ ተወቃሽ ነው" ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ሀገራዊ ለውጡ ያስኮረፈው ህወሀት ባለፉት ሁለት ዓመታት በፈጸመው ወንጀል የበርካታ ዜጎች መፈናቀልና ሰብአዊ ቀውስ እንደደረሰባቸው አውስተዋል።
የሀገር ክህደት የፈጸመው ጽንፈኛው ቡድንን ሥርዓት ለማሲያዝ መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው ለዚህም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከመንግስት ጎን በመሆን እንደሚደግፍ አስታውቀዋል፡፡