ቀጥታ፡

ለምርጫ የአየር ጊዜና የጋዜጣ አምድ ድልድል የሴትና አካል ጉዳቶች እጩ ብዛት መስፈርት እንዲታይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2013 (ኢዜአ) በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ለተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የአየር ጊዜና ጋዜጣ ዓምድ ድልድል የሴትና የአካል ጉዳተኞች ዕጩዎች ብዛት መስፈርት እንዲጤን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምና ድልድል ረቂቅ መመሪያ ላይ ከመገናኛ ብዙሃንና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ዛሬ ተወያይቷል።

ረቂቅ መመሪያው ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ውድድር ጠቅላላ የአየር ጊዜ ወይም የጋዜጣ ዓምድ የሚደለድልባቸው መርሆዎችን አስፍሯል።

የሕግ ባለሙያው አቶ ኒቆዲሞስ ጌታሁን የረቂቅ መመሪያውን ይዘት፣ ድንጋጌና ተፈጻሚነት ለተሳታፊዎቹ አብራርተዋል።

ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤቶች ባቀረቧቸው የሴት ዕጩ ተወዳዳሪዎች ብዛት መሰረት ከጠቅላላው የአየር ጊዜና የጋዜጣ ዓምድ ውስጥ 20 በመቶ እንደሚከፋፈሉ በረቂቅ መመሪያው ተቀምጧል።

በአካል ጉዳተኞች ዕጩ ተወዳዳሪዎች ብዛት መሰረት ደግሞ ከጠቅላላው የሰዓት ድልድል 10 በመቶ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚከፋፈሉ ተደንግጓል።

በአየር ጊዜ ወይም የጋዜጣ ዓምድ ድልድል ቀመሩ መሰረት ሴቶችና አካል ጉዳተኞችን ለማሳተፍ አስቻይ ሁኔታዎችን ከግምት ያስገባ ባለመሆኑ ቦርዱ ሊያየው እንደሚገባ የፓርቲ አመራሮች ጠይቀዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች በሥራ ላይ ባሉት በሕዝብ ተወካዮችና በክልል ምክር ቤቶች አባላት የመቀመጫ ብዛት አምስት በመቶ እንዲከፋፈሉ መደረጉ በጎ ቢሆንም፤ በአተገባበሩ ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ተነስቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ ወይዘሪት ሶልያና ሺመልስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያነሷቸውን ሃሳቦች ረቂቅ መመሪያውን ለማዳበር እንደ ግብአት ይታያሉ ብለዋል።

የአየር ጊዜና የጋዜጣ ዓምድ ድልድል ቀመር ፓርቲዎቹ በሚያቀርቧቸው የሴትና የአካል ጉዳተኛ ዕጩዎች ብዛት መሰረት የተደረገው ተሳትፏቸውን ለማበረታታት መሆኑንም አብራርተዋል።

ረቂቅ መመሪያው እንዳስቀመጠው ለምርጫ የሚወዳደሩ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተመደበው ጠቅላላ የመገናኛ ብዙሃን የአየር ጊዜ እንዲሁም የጋዜጣ ዓምድ ውስጥ 25 በመቶውን እኩል ይከፋፈላሉ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የአየር ጊዜ ወይም የጋዜጣ ዓምድ መጠንና የዕጣ አወጣጥ ድልድል ለማድረግ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን መተግበሪያ እያበለጸገ መሆኑን በውይይቱ ላይ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም