በትግራይ ክልል የሚገኙ ሴቶች ከጭቆና ነጻ እንዲወጡ ሴቶች አጋርነታቸውን ማሳየት እንደሚገባቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል የሚገኙ ሴቶች ከጭቆና ነጻ እንዲወጡ ሴቶች አጋርነታቸውን ማሳየት እንደሚገባቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 11/2013 (ኢዜአ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለ15ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀንን በማስመልከት "የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት" በሚል ርዕስ ለክልልና ከተማ ምክር ቤቶች እንዲሁም ለሴቶችና ህጻናት ቢሮ የስራ ሃላፊዎች ያዘጋጀው ስልጠና ተከናውኗል።
የሕወሓት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል በሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት በክልሉ ሕግ የማስከበር እርምጃ እየወሰደ መሆኑ ይታወቃል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ እፀገነት መንግስቱ የሕወሓት ቡድን ዜጎች መብታቸው እንዲጣስ፣ ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉና ግጭቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱን ገልጸዋል።
ቡድኑ ሲፈጽማቸው በነበሩ ድርጊቶች ከየትኛውም ህብረተሰብ ክፍል በበለጠ ሴቶችና ህጻናት ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሾች እንደሆኑም ተናግረዋል።
የሕወሓት ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ በትግራይ ክልል እየተወሰደ ያለው የሕግ ማስከበር እርምጃ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
በመሆኑም በተለይ ሴቶችና ወጣቶች መንግስት በወንጀለኛው የህወሃት ቡድን ላይ እየወሰደ ባለው እርምጃ አጋርነታቸውንና ድጋፋቸውን ሊያሳዩ ይገባል ብለዋል።
የሰላም መስፈንና መረጋገጥ ከማንም በላይ ሴቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በመገንዘብ ሴቶች ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸውም ምክትል አፈ-ጉባኤዋ አሳስበዋል።
በየደረጃው የሚገኙ ሴት አመራሮችም ለሰላም መስፈን የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልል ምክር ቤት እንዲሁም የሴቶችና ህጻናት ቢሮ የስራ ሃላፊዎች በትግራይ ክልል ከሚገኙ ሴቶች ህጻናትና እናቶች ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
በትግራይ ክልል እየተወሰደ ያለው እርምጃ የክልሉን ህዝብ በተለይም ደግሞ ሴቶችና ህጻናትን የሚታደግ ህግ የማስከበር ሂደት መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ያሉ ሴቶች የሕወሓት ወንጀለኛ ቡድን መደበቂያ እንዳያደርጋቸው ሊከላከሉና ለመንግስት አስፈላጊውን መረጃ ሊሰጡ ይገባልም ብለዋል።
15ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሕዳር 29 ቀን 2013 ዓ.ም "እኩልነትና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ለጋራ ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል ይከበራል።