ቀጥታ፡

ወደ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎች በአጭር ጊዜ ወደ አገራቸው ይመለሳሉ... የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2013(ኢዜአ) ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በፈጠረው ችግር ወደ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ወደ አገራቸው በመመለስ መልሶ የማቋቋም ስራ እንደሚሰራ የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ከጽንፈኛው የህወሃት ቡድን ነጻ ባልወጡ አካባቢዎች ለሚገኙ ዜጎች ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሰብዓዊ ድጋፍ ይደረጋል ተብሏል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት በህወሓት የጥፋት ቡድን ላይ ሕግ የማስከበር እርምጃ የጀመረው ኢትዮጵያና ሱዳንን በሚያዋስኑ ከተሞች አካባቢ መሆኑ በመሆኑ፤ ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ወደ ሱዳን ገብተዋል።

የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢትዮጵያ መንግስት ለዜጎቹ ደህንነትና ክብር ቅድሚያ ሰጥቶ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ኮሚሽኑ በሱዳን የሚገኙ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ወደ አገራቸው ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ነው የገለጹት።

በአሁን ጊዜ የመከላከያ ሰራዊት አብዛኞቹን የትግራይ አካባቢዎች ከጽንፈኛው ቡድን ነጻ እያወጣ ይገኛል።

ኮሚሽኑ የመከላከያ ሰራዊቱ ነጻ ያወጣቸው የትግራይ አካባቢዎች በተለይም በምዕራብና በሰሜን ትግራይ አካባቢዎች የመስክ ምልከታ የሚያደርግ ግብረ ኃይል ማሰማራቱም ተገልጿል።

ግብረ ኃይሉ የተፈናቃይ ዜጎችን ትክክለኛ ቁጥርና የሚያስፈልገውን ድጋፍ ትክክለኛ መረጃ የሚሰበስብ መሆኑም ነው የተጠቀሰው።

ይሁንና ነጻ ያልወጡ አንዳንድ አካባቢዎች ለንጹሃን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር እየተሰራ መሆኑንም ኮሚሽነር ምትኩ ገልጸዋል።

በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የተጀመረው ህግ የማስከበር እርምጃ ድጋፍ ለሚፈልጉ ዜጎች በቂ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅርቦት መኖሩንም አረጋግጠዋል።

በደቡብ ክልል ኮንሶና በቤንሻንጉል ጉምዝ መተከል አካባቢ ለተፈጠሩ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ መስጠቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ጋር ተያይዞ በርካታ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ይሻሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም