ቀጥታ፡

ህግን ለማስከበር እየተወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ በጋምቤላ የሚገኙ የቀድሞው ሠራዊት አባላት ገለጹ

ጋምቤላ፤ ህዳር 11/2013(ኢዜአ) ጽንፈኛውን የህወሓት ቡድን ስርዓት ለማሲያዝ እየተካሄደ ያለውን ሀግ የማሰከበር እርምጃ በመደገፍ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በጋምቤላ ክልል የሚኖሩ የቀድሞው ሠራዊት አባላት ገለጹ።

አባላቱ የህወሓት የጥፋት ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ድርጊት አሳፋሪ መሆኑን በመግለጽ አውግዘዋል።

በክልሉ የሚኖሩት የቀድሞው አየር ኃይል አባል የነበሩት ኡሞድ ተፋላ ለኢዜአ  እንደተናገሩት ጽንፈኛውን የህወሓት ቡድን ሰሚ ጠፍቶ እንጂ ቀድሞም ቢሆን   ገንጣይና ሀገር አፍራሽ ነበር። 

አሁንም ይህንኑ እኩይ ድርጊቱን   በገሀድ  ማሳየቱን አመላክተዋል።

ይህንን ጽንፈኛ ቡድን ሥርዓት ለማሲያዝ መንግስት ለጀመረው ህግን የማስከበር ተግባር በመደገፍ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው አስፈላጊውን  መስዋዕትነት  ለመክፈል  ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ጁንታው የሀገርን ዳር ድንበርና የህዝብን ሰላም በመጠበቅ በደስታም ሆነ በችግር  ጊዜ  ከህዝብ ጋር በነበረው የመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት መቼውንም ይቅር ሊባል የሚቻል አይደለም ብለዋል።

"ከሃዲው ህወሓት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥፋት  ጨካኝ በሚባለው የቦኮሃራም አሸባሪ ሊፈጽም የማይችለው ድርጊት ነው" ያሉት ደግሞ ሌለው የቀድሞው  ሠራዊት አባል  ሃምሳ አለቃ  ዘለቀ ደሬሳ ናቸው።

ቡድኑን ለህግ ለማቅረብ መንግስት የተጀመረው  ህግን የማስከበር እርምጃ ለማገዝ ከሀገር  መከላከያ ጎን በመሰለፍ የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ግዴታ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሌላው የሠራዊቱ አባል የነበሩት ሃምሳ አለቃ ፈረደ ደሬሳ በበኩላቸው የወያኔ ጽንፈኛው  ቡድን ክፉ ተግባሩን የሚቃወመው  ኃይል ማጥፋት የተለመደ ተግባሩ መሆኑን   ተናግረዋል።

በቅርቡም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ድርጊት የተለመደ የክፉ ተግባሩ  ማሳያ ነው ያሉት ሃምሳ አለቃው፤ ይህን ጽንፈኛ ቡድን ፍፃሜውን እንዲያገኝ የተጀመረው ህግ የማስከበር ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ  አመልክተዋል።

በተጀመረው ህግን የማስከበር ተግባርም ከሠራዊቱ ጎን በመሆን አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።

ህግን ለማስከበር መንግስት የህወሓት ጽንፈኛ ቡድን ላይ  እየወሰደ ያለውን እርምጃ  በመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ የተናገሩት ደግሞ  አስር አለቃ ፈንታሁን አራጋው ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም