አገራቱ መንግስት በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል እያካሄደ ያለው ሕግ የማስከበር እርምጃ እንዲጠናከር ይፈልጋሉ... ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
አገራቱ መንግስት በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል እያካሄደ ያለው ሕግ የማስከበር እርምጃ እንዲጠናከር ይፈልጋሉ... ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2013(ኢዜአ) የምስራቅ አፍሪካ አገራት የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል እያካሄደ ያለው ሕግ የማስከበር እርምጃ እንዲጠናከር እንደሚሹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መንግስት እየወሰደ ባለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ብዥታዎችን የማጥራት ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች፤ በኢኮኖሚ፣ በዜጋ ዲፕሎማሲና በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳዮች ያለፉትን ሁለት ሳምንታት አበይት የውጭ ግንኙነት ክንውኖችን አብራረተዋል።
ከክንውኖቹ መካከል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው ልዑክ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ጉብኝት ስኬታማ ዲፕሎማሲያዊ ክንውን እንደነበር ገልጸዋል።
ልዑኩ ጉብኝት ባደረገባቸው ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክና ዑጋንዳ ከፕሬዚዳንቶችና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃፊዎች ጋር በኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ መምከሩንም አንስተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ እየወሰደ ያለው የሕግ ማስከር ዘመቻ መነሻ፣ ይዘትና ዓላማ በዝርዝር ማስረዳቱን አብራርተዋል።
ላለፉት ሁለት ዓመታት ከመንፈቅ የህወሓትን የመንግስትን አገራዊ ሪፎርም ተቃውሞ፣ በተለያዩ የአገሪቷ አካቢዎች የሽብር አካላትን ሲደግፍ እንደነበር፣ በተደጋጋሚ የሕግ ጥሰቶች መፈጸሙንና በመጨረሻም በአገር ሉዓላዊነት ቀይ መስመር ማለፉን የአገራቱ መሪዎች እንዲገነዘቡ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በዚህም መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ የእርስ በርስ ጦርነት ሳይሆን የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባር መሆኑን ማስረዳት ተችሏል ብለዋል አምባሳደር ዲና።
የአገራቱ መሪዎችም የኢትዮጵያ ሠላምና ደህንነት ለአፍሪካ ቀንድ ሠላም መሰረት መሆኑን በመግለጽ፤ ሕግ የማስከበር እርምጃ የአገር ውስጥ ጉዳይ በመሆኑ ማንም ጣልቃ የሚገባበት እንዳልሆነ ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል።
መንግስት እየወሰደ ያለው ሕግ የማስከበር እርምጃ ንጹሃን እንዳይጎዱ ታሳቢ ተደርጎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቋማቸውን ማሳወቃቸውንም አክለዋል።
በሕግ ማስከበር እርምጃው ንፁሃን እንዳይጎዱና ማኅበራዊ ቀውስ እንዳይከሰት መንግስት እርምጃውን በጥንቃቄ እየወሰደ እንደሆነ ተገልጾላቸዋልም ብለዋል።
አምባሳደሩ ከአራቱ አገራት በተጨማሪ ለሌሎች ጎረቤት አገራትም አሁናዊ ሁኔታዎችን የማስረዳት ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም በጅቡቲና በሱዳን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደህነነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክት ማድረሳቸውንና ምክክር ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
ጎረቤት አገራቱም ከኢትዮጵያ ሠላም ጎን መቆማቸውን ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በፓስፊክ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንስላዎች እንዲሁም ግለሰቦች የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁናቴ አስመልክቶ ለአገራት መሪዎችና ሚዲያዎች ግልጽ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
በመዲናዋ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ተወካዮች በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጻ እንደተደረገላቸውም እንዲሁ።
በሌላ በኩል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ስለመቀጠሉ፣ በኢኮኖሚና ዲፕሎማሲ ረገድም ከተለያዩ አገራት ኩባንያዎች ጋር የኢንቨስትመንት ምክክር መደረጉን ገልጸዋል።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲም ከቤይሩት 83፣ ከጂዳ ከ280 በላይ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል።