በኦሮሚያ ክልልና ድሬዳዋ አስተዳደር ለሠራዊቱ 97 ሠንጋዎች ተበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልልና ድሬዳዋ አስተዳደር ለሠራዊቱ 97 ሠንጋዎች ተበረከተ
አምቦ/ነቀምቴ/ ድሬዳዋ/ ህዳር 11 /2013(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋና ምሥራቅ ወለጋ ዞኖች እንዲሁም ድሬዳዋ አስተዳደር ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚውል 97 ሠንጋዎች ተለገሰ።
ከተለገሰው ውስጥ በምዕራብ ሸዋ ዞን የደንዲ ወረዳና የኤጄርሳ ለፎ ወረዳ ነዋሪዎች የሰጡት 63 ሠንጋዎች ይገኙበታል።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አጀማ ቶለሳ ከነዋሪዎቹ የተለገሰው ድጋፍ ርክክብ በተካሄደበት ወቅት ክቡር የሆነውን የሀገር መከላከያን ነክቶ የሚያመልጥ የለም ለዚህ ነው ህዝቡ በመደገፍ አጋርነቱን እያሳየ ያለው ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ በየመንደሩ ሽብር ከሚፈጥሩ አካላት ራሱንና አካባቢውን ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።
የደንዲ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ተሾመ ጣፋ የድጋፍ ሥነ-ሥርዓቱ በጊንጪ ከተማ ሲከናወን እንደገለጹት የህወሃት ጁንታ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው አስነዋሪ ድርጊት ነዋሪዎችን አስቆጥቷል።
ይህን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎች በመነሳሳት ለሃገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን አክብሮትና ፍቅር ድጋፍ በማድረግ እየገለጹ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በተመሳሳይ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ የአንገር ጉቴ ከተማ ነዋሪዎች ለሠራዊቱ 19 ሠንጋዎችን ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን በተግባር ማሳየታቸውን የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዋስሁን ጉደታ ገልጸዋል።
የዞኑ አስተዳደሪ አቶ ደረጀ አበራ ከከተማዋ ነዋሪዎች የተበረከቱትን ሠንጋዎች ለምዕራብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ የኢንዶክትሪኔሽንና የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ተወካይ ሻለቃ ቴዎድሮስ ግዛው በማስረከብ ነዋሪዎቹ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ አህመድ ሰይድ በሰጡት አስተያየት ለሠራዊነቱ ደጀንነታቸውን ለማሳየት የሚያደርጉት ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
አቶ መልካሙ ታደሰ በበኩላቸው "ድጋፋችን ለመከላከያ ሠራዊታችን "በሚል መሪ ሀሳብ ተነሳስተው ነዋሪውን በማስተባበር ሠንጋዎቹን ገዝተው ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የድሬዳዋ አስተዳደር የብዬአዋሌ ክላስተር አርሶአደሮች ሠራዊቱ የጀመረውን ሀገርን የማዳን ዘመቻ እንዲሳካ ከ730 ሺ ብር በላይ የሚያወጡ 15 የደለቡ የሀገር ሰንጋዎች አበርክተዋል፡፡
12 የገጠር ቀበሌዎችን ያካተተው የክላስተሩ አርሶ አደሮች በአካባቢያቸው ባደረጉት ወቅታዊና ሀገራዊ ውይይት የህወሃት ሀገር አፍራሽ ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመውን የወንጀል ድርጊት አውግዘዋል፡፡
የክላስተሩ አስተባባሪ አቶ መሐዲ ዑመር እንደተናገሩት አርሶ አደሮች የሀገር መከላከያ ሰራዊት ህግን ለማስከበር እያካሄደ ያለውን ዘመቻ ለማገዝ የደለቡ የሐረር ሠንጋዎችን ለግሰዋል።
የክላስተሩ ወጣቶች አስተባባሪ ወጣት መሐመድ ዩሱፍ መንግስት ጥሪ ቢያስተላልፍልን ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ለመዋጋት ተዘጋጅተን እየጠበቅን ነው ብሏል፡፡
የሴቶች ተወካይ ወይዘሮ ኑሪያ አልይ በበኩላቸው ለሠራዊቱ የሚደረገው ድጋፍ ስሜታችንን ለመግለጽ እንጂ በቂ አይደለም፤ አካባቢያችንን ተደራጅተን በጥንቃቄ እየጠበቅን ሠራዊቱን እያገዝን እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል።
በኢፌድሪ አየር ኃይል የምስራቅ አየር ኃይል ምድብ ዋና አዛዥ ኮረኔል አበበ ለገሰና የምስራቅ ዕዝ ደረጃ ሶስት ሆስፒታል አዛዥ ተወካይ ሌተናል ኮረኔል ብርሃኑ ዘውዴ ድጋፉን በመረከብ ምስጋና አቅርበዋል።