ቀጥታ፡

የህወሃት ቡድን የሚነዛውን የውሸት ፕሮፖጋንዳ በመቀልበስ እውነታውን ለአለም ማህበረሰብ ለማስረዳት እየተሰራ ነው

ባህር ዳር፣ ህዳር 11/2013(ኢዜአ) የህወሃት አገር አፍራሽ ቡድን ለአለም አቀፉ ማህበረሰቡ እያሰራጨ ያለውን የውሸት ፕሮፖጋንዳ በመቀልበስ እውነታውን ለማስረዳት እየሰሩ መሆናቸውን በቻይና ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ኢትዮጵያዊያን ገለጹ።

እነዚህ የአማራ ክልል ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ህግን ለማስከበር ለተሰማራው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ  ድጋፍ የሚሆን ከ148 ሺህ ብር በላይ  ለግሰዋል።

የተማሪዎቹ ተወካይ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ  አየነው በላይ እንደገለጹት የህወሓት ከሃዲ ቡድን  በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው የክህደት ወንጀል  በቻይና  የሚማሩ ኢትዮጵያዊያንን አስቆጥቷል።

ህወሃት ላለፉት ሁለት ዓመታት የጦርነት ነጋሪት ቅስቀሳዎችንና ዝግጅቶችን ሲያደርግ መንግስት ጉዳዩን  በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት  ለመፍታት ፍቃደኝነቱን ሲያሳይ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ሆኖም ዘራፊው ቡድን በህዝብ ትግል ያጣውን ስልጣን በጉልበት መልሶ ለማያዝ በፈጠረው ትንኮሳ  እየተሸነፈ ቢሆንም በውሸት ፕሮፖጋንዳ የዓለምን ህዝብ እያደናገረ ይገኛል ብለዋል።

በቻይና የሚማሩ ኢትዮጵያዊያን  የተለያዩ የትስስር ገጾችን በመጠቀም  የጥፋት ቡድኑ የሚነዛውን የውሸት ፕሮፖጋንዳ በመቀልበስ እውነታውን ለአለም ማህበረሰብ ለማስረዳት እየሰሩ  መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ውጤት እየተገኘ መሆኑን አመልክተው  የቻይና ህዝብና መንግስት እውነታውን እየተረዱ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጓዳኝም በቻይና  ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ 73 ተማሪዎች ለቀለብ ከሚሰጣቸው የወር ወጪ  በመቀነስ 148 ሺህ 445 ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ህወሃት ለዘመናት የቻይናን ኤምባሲ በበላይነት ተቆጣጥሮ በመቆየቱ የቻይና መንግስትና ህዝብ ስለቡድኑ  የተሻለ ግንዛቤ እንዳላቸው  የገለጹት ደግሞ ሌላኛው ተወካይ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ  ዘውዱ ሙጨ ናቸው።

ለትምህርት ወደ ቻይና የሚላኩ የትግራይ ተወላጆች ሳይቀር የሄዱበትን ተልኮ ትተው የፖለቲካ ስብሰባ ሲያደርጉ እንደነበርም ጠቁመዋል።

ህወሃት በተለይም ለኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር የሆነችውን ቻይናን በውሸት ፕሮፖጋንዳ ጠምዝዛ በመያዝ  የቻይና ህዝብና መንግስት ለቡድኑ የተለየ ትኩረት እንዲሰጥ ሲያደርግ እንደኖረ አስረድተዋል።

ዛሬም በዓለም ላይ ተደርጎ የማይታወቅ የራሱን   መከላከያ ሠራዊት  ከጀርባ ሆኖ  ማጥቃቱ ሳያንስ እንደተበደለ የውሸት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት እውነታውን ለማሳሳት እየጣረ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን የውሸት ፕሮፖጋንዳ በማጋለጥ እውነታውን ለማስረዳት የተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ድህረ ገጾች በመጠቀም በበቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ  አማካኝነት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም  የቻይና መንግስትና ህዝብ እውነታውን እየተገነዘቡ እንዲመጡ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ሌላው በቻይና የሶሰተኛ ዲግሪ ተማሪው ግርማ መለሰ በበኩላቸው ''ህወሃት በመከላከያ ስራዊት ላይ የፈጸመው ግፍ በትምህርትም ሆነ በሌላ መስክ በውጭ  የምንኖር ኢትዮጵያዊያንን አንገት አስደፍቷል'' ብለዋል።

በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ኢትዮጵያ በውጪ ለሚኖሩ ዜጎቿ የኩራት ምንጭ ሆኖ ሳለ ህወሃት በጠላትነት ተነሳስቶ  በራሱ የመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው ወንጀል አሳፋሪ መሆኑን  ገልጸዋል።

ህወሃት በራሱ ጊዜ በፈጠረው ትንኮሳ  ግብዓተ መሬቱ እየተፋጠነ መሆኑን  አመልክተው "በቻይና ሀገር የምንኖር ተማሪዎች የህወሃትን የውሸት ፕሮፖጋንዳ በማስተባበል የዜግነት ግዴታችን እየተወጣን ነው ብለዋል።

ይህን ሃገር አጥፊ ቡድን ሥርዓት ለማሲያዝ በሚደረገው ህግ የማስከበር እንቅስቃሴ ለዓለም ማህበረሰብ እውነታውን ከማስረዳት ባለፈ በግንባር ለተሰለፈው ህግ አስከባሪ ሀይል የጀመሩትን ድጋፍ   አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

የክልሉ ድጋፍ አሰሰባሳቢ ኮሚቴ ተወካይ  አቶ አታላይ ጥላሁን በበኩላቸው  ህግን ለማስከበር ለተሰማራው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ሀይልና ሚሊሻ  እየተደረገ ያለው ድጋፍ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ድጋፍ በሀገር ውስጥ እና  ውጭ ጭምር  በጥሬ ገንዝብ እና ዓይነት እየቀረበ መሆኑን  አስረድተዋል።

በቻይና የሚኖሩ የክልሉ ተወላጅ ኢትዮጵያዊያን ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም