የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች ለተቸገሩ ታዳጊዎች የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች ለተቸገሩ ታዳጊዎች የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 11/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች ወላጆቻቸው አነስተኛ ገቢ ላላቸው ታዳጊ ሕጻናት የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።
የተቋሙ የሴቶችና ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ታደለች ቦጋለ እንዳሉት ድጋፉ የተደረገው ወላጆቻቸው አነስተኛ ገቢ ላላቸው 18 ታዳጊዎች ነው።
የተቋሙ ሠራተኞች ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ለታዳጊዎቹ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው በየዓመቱ መጀመሪያ የተደረገውን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለአብነት ጠቅሰዋል።
ለታዳጊዎቹ ድጋፍ ለማድረግ የሚወጣው ገንዘብ ሠራተኞቹ በየወሩ ከደመወዛቸው የሚያዋጡት መሆኑን ገልጸዋል።
የምግብና የቁሳቁስ ድጋፉ ትምህርት ቤት እስከሚከፈት ድረስ ለልጆቹና ለወላጆቻቸው አስፈላጊ መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ታደለች፤ በቀጣይም እገዛ የሚደረግላቸውን ሕጻናት ቁጥር ለመጨመር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ከታዳጊዎቹ ወላጆች መካከል ወይዘሮ ሃሴት ደጀኔ በልብስ አጠባ እንደሚተዳደሩና የአራት ልጆች እናት መሆናቸውን ገልጸው፤ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሥራ በማቆማቸው ኑሮ እንደከበዳቸው ገልጸዋል።
ወይዘሮ ሃሴት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች ከዚህ ቀደምም ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርጉላቸው እንደነበር አስታውሰዋል።
በኮሮናቫይረስ ምክንያት ትምህርት መቋረጡን ተከትሎ የትምህርት ቤት ምገባ በመቆሙ ልጆቻቸው ለችግር ተዳርገው በመቆየታቸው የተደረገላቸው ድጋፍ እንዳስደሰታቸውም ገልጸዋል።
ወይዘሮ መልሽ ተስፋዬ በበኩላቸው ለሁለት ዓመታት በተቋሙ ሠራተኞች ድጋፍ ሲደረግላቸው እንደነበረና ይህም ችግራቸውን እንደሚያቃልልላቸው ተናግረዋል።
የዓለም ሕጻናት ቀን ከሕዳር 9 እስከ 11 ቀን 2013 ዓ.ም "ትውልድን እንቅረፅ አገርን እንታደግ" በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው።