ቀጥታ፡

ሕግና የአገር ሕልውና በማስከበር ዘመቻ ላይ ለሚገኘው ሠራዊት ድጋፋችንን እናጠናክራለን - የኦሮሚያ ክልል ተወካዮች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 11/2013 (ኢዜአ) በሕግና በአገር ሕልውና ማስከበር ዘመቻ ላይ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ተወካዮች ገለጹ።

ከኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን የመጣው ወጣት አብዱላሂ መሐመድ ህወሓት የራሱን ሥልጣን ለማራዘም የኦሮሞና የሶማሌ ብሄረሰቦችን በማጋጨት ደም ሲያራጭ ዓመታትን አስቆጥሯል ይላል።

ይህ አልበቃው ብሎት "እኔ ካልገዛሁ ኢትዮጵያ ትፈራርስ" በሚል ራስ ወዳድ አመለካከት አገር ለማፈራረስ ቀይ መሥመሩን አልፎ የአገር ደጀን በሆነው መከላከያ ሠራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን አስታውሷል።

በመሆኑም በዚህ የህወሓት ቡድን ላይ የሚወሰደውን ሕግ የማስከበር እርምጃ በማንኛውም መልኩ እደግፋለሁ ሲል ተናግሯል።

ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ለሰራዊቱ ድጋፍ በማሰባሰብ መዳረሻቸውን በአማራ ክልል ቆቦ ከተማ ያደረጉ አባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎችም ድጋፉ ይቀጥላል ብለዋል።

በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የደረሰው ጥቃት የመላው ኢትዮጵያዊያን ጥቃት መሆኑን የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ ከሠራዊቱ ጎን መቆም የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል።

አባቦኩ ብርሃኑ ኡርጋ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የደረሰውን ጥቃት ለመቃወምና ከሰራዊቱ ጎን መሆናችንን ለመግለጽ ነው የመጣነው ብለዋል።

አቶ ጀማል ሁሴን በበኩላቸው ከሰራዊቱ ጎን በመቆም ማንኛውንም አይነት የገንዘብም ሆነ የቁሳቁሶች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

"ድል ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድል ለመከላከያ ሰራዊታችን ድጋፋችን ይቀጥላል” ሲሉ የተናገሩት ደግሞ ሐዩ ካሱ ገብሩ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም