ቀጥታ፡

እነርሱ ለእኛ ዕድሜ ልካቸውን፤ እኛ ደግሞ ለእነርሱ ሁለት ደቂቃ ብቻ ቆመናል

መንግስቱ ዘውዴ(ኢዜአ)

እነርሱ ለደቂቃ እንኳ አይተኙም፣ የግል የሚባል ሕይወት አጣጥመውም ኖሯቸውም አያውቅም፣ ደስታቸውና ስኬታቸው የኢትዮጵያ ክብር እንዳይደፈር ሁሌም በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንኳን ስለ ክብሯ ዘብ መቆም ነው፡፡ በየተሰማሩበት የግዳጅ ቀጣና ሁሉ ድንጋይ ተንተርሰው፣ የኮዳ ውሃ ተጋርተው፣ ሀገርን ይጠብቃሉ፣ ወገንን ያኮራሉ፡፡ እነርሱ ሀገርንና ሕዝብን በማስቀደም ሁሌም  ደጀን ሆነው ይቆሙልናል፡፡ ከፈጣሪ በመቀጠል በምድር ያሉን መከታዎቻችን እነርሱ ናቸው፡፡ በምድር ላይ ከእነርሱ ውጭ መከታም፤ ጋሻና ምሽግም የለንም፡፡

እነዚህን የሀገር መከታዎች የውጭ ጠላት በተዳጋጋሚ ሞክሯቸው ሁሉም እሳት የሆነ ክንዳቸውን ቀምሶ ወደ መጣበት በሽንፈት እንዲመለስ ሆኗል፡፡ አሁን ላይ ግን መሆን ያልነበረበት፤ ክስህተቶች ሁሉ የከፋው ስህተት በህወሃት የጥፋት ቡድን ተሰርቷል፡፡  በህወሃት የጥፋት  ቡድን ተዋጊ ጦር ጥቃት ተፈጽሞበታል፡፡ ምንም እንኳን ሰራዊቱ ለበርካታ ዓመታት እዛው ህብረተሰቡ ውስጥ ሆኖ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ሲያግዝ የቆየና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያበረክት የነበረ ሰራዊት ባጎረሰ ቢነከስም፣ ከዚህ ህዝባዊነት መንፈሱ መቼምና በምንም ምክንያት ለደቂቃም ቢሆን ዝንፍ እንደማይል ይታወቃል፡፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለአንድ ሀገር የመኖር ህልውና ያለውን ጠቀሜታ በጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚደንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ «የመከላከያ ሠራዊት የአንድ ሀገር ደም ስር ነው፤ ደም ሥር ውስጥ ደም ኬሌለ ሕይወት የለም» ሲሉ ገልጸውታል፡፡ የአንድ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ማለት ከፈጣሪ በታች ሀገሪቱን ከተለያዩ ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ አደጋዎች የሚጠብቅ የመጨረሻ ደጀን ነው፡፡ ይህንን መሰራታዊ መርህ በሳተ መልኩ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሀገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ጥቁር ጠባሳ ተከስቷል፤ በዚህ ዕለት ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ30 አካባቢ ለራሱ ህይወት ሳይሰስት ስለሀገሩና ህዝቧም ደህንነት ዋጋ እየከፈለ ባለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ተፈጸመበት፡፡

ድርጊቱ የተፈጸመው ባህር አቋርጦ ድንበር ጥሶ በመጣ ወራሪ ኃይል ወይም በቅኝ ገዥ አካል አልነበረም፡፡ ይልቁንም ቀን በሐሩር ሌሊት በቁር ደህንነቱን ሲጠብቅለት ህልውናውን ሲያረጋግጥለት በኖረው በራሱ  ወገን አኩራፊ ቡድን መሆኑ የህዝቡ ቁጣ ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

የሀገር ደጀን፤ የህዝብ አለኝታ፤ የድንበር መከታ በሆነው የሀገር መከለከያ ሰራዊት ላይ እንዲህ ያለ ነውረኛ ጥቃት የፈጸመው ህገ-ወጥ አካል ላይ መላ ኢትዮጵውያን ቁጣቸውን እንዲያሰሙ አስገድዷቸዋል፡፡ ይህ ቁጣና ውግዘት በሀገር ውስጥ ብቻ የታጠረም አልነበረም። ይልቁንም አሜሪካና ጀርመን የህወሃት የጥፋት ቡድን ታጣቂዎች ወደ ኤርትራ ያስወነጨፉትን ሚሳኤል እና በፌዴራል መንግስቱ እና በህወሃት የጥፋት ቡድን  መካከል እየተደረገ ያለውን ውጊያ ዓለማቀፍ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ በአጥፊው ቡድን እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚያወግዙ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው በኩል መግለጻቸውና የበርካታ ሀገራት መሪዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር አውግዘዋል። በኢፌዴሪ መንግስት የተጀመረውን ህግ የማስከበር እና የህልውና ዘመቻን በህዝብ ለህዝብ መካከል ወይም የእርስ በርስ ጦርነት እንዲሁም በአጠቃላይ ቀጣናዊ ቀውስ የሚፈጥር አስመስሎ ለማቅረብ በቡድኑ በኩል እየተሰራ ያለውን ድብቅ ስራ ለአደባባይ አጋልጦ ያሳየ፤ በአንጻሩ የፌዴራል መንግስቱ እየወሰደ ያለው እርምጃ ከህግ አንጻርም ሲፈተሸ ፍትሃዊ እርምጃ እንደሆነ በህግ ምሁራን በኩል መረጋገጡ፤ ጉዳዩን ኢትዮጵያውያንና መላ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ እንዲያውቁት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

የጥቃቱን መፈጸም ተከትሎም መላ ኢትዮጵያውያን ከመጠቃት ቁጭት ባለፈ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ክብር߹ ፍቅርና ድጋፍ በተለያየ መንገድ እየገለጹም ይገኛሉ፡፡

የድርጊቱ ጸያፍነት፤ የጥቃቱ ጉዳትና ነውርነት ሳይዘነጋ ክስተቱን ተከትሎ መላ ሕዝቡ ያሳየው ድጋፍ ኢትዮጵያውያን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ አሁንም በሀገራቸው ሉዓላዊነት߹ በክብራቸውና ብሄራዊ ጉዳያቸው ምን ያህል ጠንካራ አቋምና አንድነት እንዳላቸው የታየበት አጋጣሚም ነው፡፡

በተጨማሪ ህዳር 8/2013 ዓ.ም በኪነጥበብ ባለሙያዎች ጠንሳሽነትና አዘጋጅነት «ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ክብር እቆማለሁ» በሚል መሪ ቃል ለመከላከያ ሰራዊቱ ታላቅ ሀገራዊ የምስጋና߹ የወገንተኝነት እና የደጀንነት መልዕክቶች የተንጸባረቁበት ሀገራዊ መርሀ-ግብር ተካሂዷል፡፡

የኪነጥበብ ባለሙያዎቹን ጥሪ በመቀበል ረገድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድን  የቀደመ አልነበረም፡፡ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ «ማክሰኞ ኅዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም "ለሀገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ" በሚል ርዕስ የ2 ደቂቃ ፕሮግራም እንዲኖር በኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጥሪ እኔም ተቀብያለሁ።» ሲሉ የገለጹ ሲሆን በዚህም «ይህ ሥነ ሥርዓት በየአካባቢያችሁ፣ በየመሥሪያ ቤታችሁ፣ በየድርጅታችሁና በየቤታችሁ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን የበኩላችሁን እንድታደርጉ አሳስባለሁ።» ሲሉም ለመላ ህየኢትዮያ ህዝብ መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡

የጠቅለይ ሚኒስትሩን መልዕክትና ጥሪ በመቀበልም በሁሉም የፌዴራል ተቋማት፤ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፤ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በዋና ዋና አደባባዮች፤ በገበያ ስፍራዎችና ሞሎች፤ በየመኖሪያ መንደሮችና በአጠቃላይ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ በአንድ አይነት ስሜት߹ በአንድ አይነት መልዕክትና በተመሳሳይ ሰዓት በድምቀት ተከብሯል፡፡

የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስቴር ሁነቱን ባከበረበት ወቅት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል  “ለመከላከያ ሰራዊታችን ከጉልበቴ ዝቅ ብዬ አክብሮትና ምስጋናዬን አቀርባለሁ” በማለት ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ታላቅ ክብር߹ ፍቅርና አክብሮት በተግባር ሳዩበት ሁነትም ነበር፡፡

ሚኒስትሯ በመልዕክታቸው “እራሱን ሰውቶ እኔ፣ አንቺ፣ አንተ፣ እኛ ኢትዮጵያ፣ ታፍረንና ተከብረን እንድንኖር ራሱን ሁልጊዜ ቤዛ ላደረገው የመከላከያ ሰራዊታችን ከጉልበቴ ዝቅ ብዬ አክብሮትና ምስጋናዬን አቀርባለሁ።” ሲሉም አጋርነታቸውን ደም በመለገስ ጭምር በተግባር አሳይተዋል፡፡

ሀገራዊ ሁነቱ በተከናወነባቸው አካባቢዎች ሁሉ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ሰንደቅ-ዓላማ በመያዝ ለመከላከያ ሰራዊታችን ያላቸውን ክብር߹ ፍቅርና አጋርነት በመግለጽ ሰራዊቱ ለበለጠ ድልና ስኬት እንዲበቃ አቅም ሊሆኑ የሚችሉ መልዕክቶችን በመያዝ፤ ልዩ ልዩ ሀገራዊ ዜማዎችን በመዘመር ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ክብር ገልጸዋል፡፡ 

በነበረው ሥነ-ሥርዓት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት የፈጸመውን ከሃዲ የህወሀት ቡድንን በግልጽ አውግዛዋል፡፡ ይህ ሀገራዊ ሁነት በድምቀት ከተከናወነባቸው አካባቢዎች መካከል አዲስ አበባ አንዷ ስትሆን አከባበሩም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም፤ በዋና ዋና አደባባዮች እና የንግድ አካባቢዎች የተከናወኑትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተከናወነው መርሃ-ግብር ላይ የከተማዋ  ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች የተገኝተዋል። በሁነቱ ላይ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በስፍራው ለተገኙ ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር «በአስቸጋሪ ወቅትና በፈታኝ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ትናንትም ዛሬም በአንድነት በአንድ ላይ የመቆም ልምድ አላቸው፤ እኛ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ጊዚያት ፈታኝ ሁኔታዎችን አልፈናል፤ ይህ ስኬት ዛሬም እንደትናንቱ እንደግመዋለን » ብለዋል፡፡

በሁነቱ ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያንም «በታሪክ በውጭ ኃይል እንኳን ያልተደፈረች፤ በየጊዚያቱ የገጠሟትን የውጭ ወረራዎችን ድል ያደረገች ሀገር በራሷ ባንዳ ቡድኖች ጥቃት መፈጸሙ አሳዝኖናል» ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ «ባለፉት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የሀገር አንድነት ስጋት ሆኖ የዘለቀው የህወሃት ዘመን አስተዳደር እንዲደገም እድል መስጠት የለብንም» ሲሉም ስሜታቸውን የገለጹም ነበሩ፡፡

በመላ ሀገሪቱ በተከናወኑ የክብር መግለጫ ሥነ-ሥርዓቶች ወቅት ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትና የኢትዮጵያዊነት ስሜቶች ጎልተው መውጣት ችለዋል፡፡ በዚህ ሀገራዊ ሁነት ላይ ሲሳተፉ የነበሩ ሰዎች አሁን ላይ መንግስት ህግን ለማስከበር እየወሰደ ባለው እርምጃ ደስተኞች መሆናቸውንና ከእነርሱ የሚጠበቀውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ከመንግስት ጎን መቆማቸውን በተለያዩ መልዕክቶች አንጸባርቀዋል፤ ከመልዕክቶቹም መካከል «መንግስት የሀገር ስጋት߹ የዜጎች ጠላት በሆነው ባንዳ ላይ እየወሰደ ያለው ህግ የማስከበርና በቁጥጥር ሥር የማዋል ዘመቻውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ለዚህም ከመንግስትና ከመከላከያ ጎን እንቆማለን» የሚሉ ነበሩ፡፡

ይህ ደማቅ ሀገራዊ ሁነት በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በስፋት የተከናወነ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ለሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ያላቸውን ክብርና ድጋፍ ከመግለጽ ባሻገር አቅማቸው በፈቀደ ሁሉ የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ተነሳሽነታቸውን የገለጹበት ሁነትም ሆኖ ታይቷል፡፡

ይህ ሀገራዊ ሁነት በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት እና በተለያዩ የክልሉ ዞኖችና ከተሞች በደማቅ ሁኔታ የተከናወነ ሲሆን በዚህ በአዲስ አበባ በሚገኘው የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር ጽ/ቤት በተከናወነ መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ « ስግብግቡ የህወሃት ጁንታ ባለፉት አመታት በኦሮሞ ህዝብ  ላይም ሆነ  እንደ ሀገር ላደረሳቸው ዘግናኝ የሆኑ ግፎች የእጁን ማግኘት  አለበት፤ የህወሃት ቡድን በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃት የሚያሳዝንና መቼም ይቅር የማይባል እንዲሁም አረመኔው የህወሃት ቡድን ከዚህ የውድቀት ጫፍ ላይ የደረሰውም በብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰው  በደል ነው።» ሲሉም ተደምጠዋል።

የሶማሊ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀሙድ እና የካቢኔ አባሎቻቸው በተገኙበት «ለሀገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ» መርሀ ግብርን ያከናወኑ ሲሆን ከሁነቱ ጎን ለጎንም ድጋፍ አድርገዋል፡፡ በዚህም ክልሉ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚውል የ10 ሚልዮን ብር ፣ 2 ሺህ የፍየል እና ከብት ድጋፍም አበርክተዋል።

በጋምቤላ ክልልም እንዲሁ «ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃት መላው የጋምቤላ ህዝብን ያስቆጣ» መሆኑን የጋምቤላ ክልል  ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገልጸዋል፡፡ ርዕሰ-መስተዳድሩ በሁነቱ ላይ ባደረጉት ንግግር «ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ክብር መቆም ለራስ ክብር እንደመቆም ሊቆጠር ይገባል» ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ ይህ የህዝቡ አለኝታነት መግለጫ እንዲሆንም ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የደም ልገሳ መርሃ-ግብር መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል "ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ክብር እቆማለሁ" በሚል መሪ ቃል መርሃ-ግብሩ የተከናወነ ሲሆን በሁነቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልሉ የጸጥታ አካላት፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የመንግስት ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆን ነዋሪዎቹም የሀገር ሰንደቅ-ዓላማን ከፍ በማድረግ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ክብርና አጋርነት አሳይተዋል፡፡

በአሶሳ በተከናወነው ሁነት ላይ የታደሙት የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሀሰን እንደተናገሩት፤ «የህወሓት ጁንታ ቡድን ሀገሪቱን ለማተራመስ በጠነሰሰው ሴራ በመተከል ዞንም ላለፉት ሁለት ዓመታት ጥፋት ሲፈጽም ቆይቷል» ያሉ ሲሆን «የጁንታው ሴራ የመንግስትን አቅም በማዳከም ሀገርን መበታተን ነው፡፡» በማለት፤ የበርካታ ዜጎች ሕይወት አለአግባብ እንዲጠፋ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተመሣሣይ በሀረሪ ክልል የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እና የካቢኔ አባሎቻቸው እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት "ሁሉን አቀፍ ድጋፋችን ለመከላከያ ሰራዊታችን" በሚል መሪ ቃል ለመከላከያ ሰራዊት ልባዊ ምስጋናና ድጋፋቸውን በመግለጽ  በሀገራዊና ክልላዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በማካሄድ ሁነቱን አከናውነዋል፡፡

በተመሳሳይ በአማራ፤ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች፤ አፋር፤ በሲዳማ ክልሎችና በድሬዳዋ አስተዳደር «ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ክብር እቆማለሁ» በሚል መሪ ቃል በሁነቱ  ላይ አባ ገዳዎች߹ ኡጋዞች߹ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞች በባህርዳር ሙሉዓለም አዳራሽ በደማቅ ሁኔታ የተከናወነ ሲሆን በተለይ በባህር ዳርና ጎንደርን ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች መርሃ ግብሩ ተከናውኗል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የመከላከያና የክልሉ ልዩ ሃይል አመራሮች እና አባላት የተሳተፉበት ነበር፡፡

ከሀገር ውጭም የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ቆንጽላ ጽ/ቤቶች በሚገኙባቸው በርካታ ሀገራት ሁነቱ በደማቅ ሁኔታ የተከናወነ ሲሆን፤ ከአፍሪካ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ߹ በሱዳን፣ በኬንያ ናይሮቢ߹ በኡጋንዳ ካምፓላ እና በግብጽ ካይሮ߹ ከመካከለኛው ምስራቅ በእስራኤል߹ በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ እና በኳታር ዶሃ፤ ከአውሮፓ በእንግሊዝ ለንደን߹ በሩሲያ ሞስኮ߹ በቤልጂየም ብራሰልስ߹ በጣሊያን߹ በፈረንሳይ߹ በስዊድን እና በጀርመን በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ቆንጽል ጽ/ቤቶች ሁነቱን በደማቅ ሁኔታ በማከናወን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ክብር፣ ፍቅርና ድጋፍ ገልጸዋል፡፡

በሱዳን በአብዬ ግዛት በሰላም ማስከበር ግዳጅ ላይ የሚገኙ የስምንተኛ ዙር ሁለገብ ሎጅስቲክስ ሰላም አስከባሪ የሰራዊት አባላት "ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ክብር እቆማለሁ" ሲሉ ጓዶቻቸውን አስበዋል፡፡ አባላቱ በዚህ ወቅት እንዳሉትም በሀገር አቀፍ ደረጃ ዛሬ መላው ህዝብ ለሰራዊቱ የሰጠውን ክብር የደገፉ ሲሆን አባላቱ ህግን ለማስከበርና የህልውና ዘመቻውን በጀግንነት እየፈፀሙ የሚገኙ ጓዶቻቸውን ለአንድ ደቂቃ አስበው ውለዋል።

የሀይማኖት ተቋማት እና አባቶችም ጭምር "ከሀገር መከላከያ ጎን እንቆማለን" በሚል ለሰራዊቱ ያላቸውን ድጋፍ እንዲሁ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች አሳይተዋል፡፡ በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት በተለያዩ ክንውኖች ሁነቱን አክብረው ውለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉ የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ሁሉ በሚነግዱባቸው ቦታዎች ሁሉ ሁነቱን በደመቀ መልክ አክብረው ውለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት  ከጥንት ጀምሮ ክንዱ ምን ያህል ከረመጥ የሚፋጅ መሆኑን በየጊዜያቱ ሀገሪቱን ለመውረርና ለማንበርከክ የሚመጡ የውጭ ጠላት ሀይሎችን ሁሉ እንዴት ባለ ከፍተኛ የጀግንነት ወኔ እያሳፈረ ሲመልስ እንደቆየና አሁንም ያለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የዛው የቀድሞ ሰራዊት የወኔ መንፈስ በመውረስ እዚህ የደረሰ መሆኑን የሰራዊቱን የተጋድሎ ውጤታማነትን በቅርብ የሚያውቁ የሁነቱ ታዳሚያን ሲገልጹም ተደምጠዋል፡፡

እንደ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚደንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ አገላለጽም «ሲሞግቱን እንረታቸዋለን፣ ሲገጥሙን እንመታቸዋለን፣ ሲገምቱን ከአቅም በላይ እንሆንባቸዋለን  ኢትዮጵያዊያን ለጠላት አንመችም፡፡» ፕሬዚደንቱ አክለውም«አፈጣጠራችን ለጣለት መብረቅ ለወዳጅ መረቅ ነው፡፡» በማለት የመከላከያ ሰራዊታችንን አይበገሬነት ገልጸውታል፡፡

ኢትዮጵያ በየዘመኑ በሚነሱ የውጭ ሃያላንም ሆኑ ሌሎች ሀገራት ፍላጎቶቻቸውን በሀይል ለማስፈጸም ሲያቅታቸው በውስጥ ያሉ ያኮረፉ አማጺንን እንደመሳሪያ በመጠቀም ለማሳካት እየሞከሩ እዚህ መድረሳቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የህንንም ለማጽናት «ዓለም ኢትዮጵያን የሚያሸንፍበትን አማራጭ ሁሉ ሞክሯል አንዱም አልተሳካም፡፡ ቀሪ ያልሞከሯቸው ነገሮች ካሉም አይሳካም፡፡ ስለማይችሉን አይወዱንም፤ ስለሚፈልጉን አይተውንም፤ ስለማይሆንላቸው አያሸንፉንም፤ አፈጣጠሯና አኗኗሯ ሚስጥር ነው፡፡ ሚስጥሩን የሚፈታው ደግሞ የሚጥሩ ባለቤት ብቻ ነው፡፡ ሌላው ዘበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የተኮሱ ተመለሱ፣ ተደመሰሱ፣  ያሴሩ ተቀበሩ፣  ታሪክ የሚያሳየው ይሄን ነው፡፡ ለጠላት መጋኛ የሆነ አርበኛ መውለድ አዲሷ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ወታደር የማይሰበር አጥር፣ የማይመለስ ግንባር፣ የማይፈታ ሚስጥር፣ ዝቅ የማይል ክብር ያለው ለአሸናፊነት ብቻ የተፈጠረ ነው፡፡ ዘምቶ ተሸንፎበት የመጣ የጦር ግንባር የለም፡፡» ሲሉ ነው ልጅ ዳንኤል ጆቴ የኢትዮጵያን߹ የመከላከያ ሰራዊቷንና የህዝቦቿን ጥብቅ ጥልቅና ሚስጥራዊ ጥንካሬ የገለጹት፡፡

አሁን ላይ ሀገሪቱ ከውስጥ የደረሰባትን ጥቃት በመመከት ረገድ የመከላከያ ሰራዊቱ እያከናወነው ያለውን ህግ የማስከበር ዘመቻን በተመለከተ «በሁሉም አሸንፎ ሁሉንም አክሽፎ ነው» የሚመጣው ሲሉ የገለጹ ሲሆን፤ ይህ አሸናፊነትን ከዘር የወረሰው ሠራዊት አሁንም ለሌላ አሸናፊነት እየተጓዘ እንደሆነ ተገልጿል፡፡  የውስጡን አረም ነቅሎ የውጭውን አረም ከድንበር ማዶ ለማስቀረት ወደ ፊት እየገሰገሰ መሆኑን ነው በተለያዩ አካባቢዎች ሁነቱን ሲያከብሩ የነበሩት የህብረተሰብ ክፍሎች አስተያየቶችን ሲሰጡ የነበረው፡፡

በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይና ስለ ኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ጀብደኝነት ከአንድ የሀገራችን ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማሕበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን «የኢትዮጵያ አርበኞች በጀግንነት ለሀገራቸው መሥዋት ሲሆኑ የኖሩ ናቸው፤ አሁን ያለው ሠራዊት የእነዚያ ጀግኖች ልጅ ነው ይሉታል፡፡ የእነዚያ ልጆች የአሁኖቹ ሠራዊቶች በስነመግባር፣ ሀገርን በመጠበቅ፣ ሕግ በማስከበርና ሀገር ባለማስደፈር ወኔ የተላበሱ ናቸው» ይላሉ፡፡  

አሁን ላይ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በህወሃት ጁንታ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ ተገቢነትና ፍትሃዊነት በማስመልከትም «በየኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተነክቶ ነው የተነሳው፣ ሳይነኩት አልነካቸውም አሁን ሀገርን የማዳን ሥራ እየሰራ ነው፡፡ ሕዝቡንና ጦሩን ያስቆጣውም አታለው መውጋታቸው ብቻ ነው» ሲሉ ተገቢነቱን አጽንኦት አንስተዋል።

ይህ በሀገር አቀፍ ደረጃ ህዝቡ በአንድ መንፈስ በመነሳት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያለውን ክብርና ፍቅር እንዲሁም ያሳየው የደጀንነት ምልክት ኢትዮጵያውያን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ክብር የገለጹበት መርሀ-ግብር ብቻ ሳይሆን ለሰራዊቱ ተጨማሪ አደራ እንደተሰጠው እንደሚቆጥሩት እንዲሁም ለቀጣይ ድል አቅምና ብርታት እንደሚሆናቸውም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ለበለጠ ግዳጅና ጀግንነት አነሳስቶናል ሲሉ ከመላ ህዝቡ ጋር በሁነቱ ላይ ሲሳተፉ የነበሩ የመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖችና አባላት ተናግረዋል፡፡

ሀገራዊ ሁነቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተወጥኖ ሰፊ ርብርብ  የታየበት እንዲሁም በጣም ስኬታማ በሆነ መልኩ እንዲከናወን መቻሉ ደግሞ ሌላኛው የህዝቡ ሀገራዊ ስሜትና አንድነት ማሳያ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም