ቀጥታ፡

ወጣቶች በአገረ መንግስት ግንባታ በንቃት እንዲሳተፉና የአገራቸውን ጉዳዮች አውቀው እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ህዳር 10/2013 (ኢዜአ) ወጣቶች በአገረ መንግስት ግንባታ በንቃት እንዲሳተፉና አገራቸውን የተመለከቱ ጉዳዮችን አውቀው እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ቀረበ። 

መስዋዕትነት ከፍለው ያመጡት ለውጥ መንገዱን እንዳይስት ጠብቀው ማቆየትና የአገራዊ ለወጡ ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸውም ተገልጿል።

"ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የወጣቶች ትግል በብዝሃነት ላይ ለተመሰረተ አገራዊ አንድነት ግንባታ" በሚል ርዕስ ለከፍተኛ አመራሮች የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት በተዘጋጀው ስልጠና የክልልና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎችና አመራሮች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ጽሁፍ ያቀረቡት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲፕሎማሲና የውጭ ጉዳይ አማካሪ አቶ ሌንጮ ባቲ እምቅ ጉልበት ያለበትን የወጣትነት ዕድሜ ለአገረ መንግስት ግንባታ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ወጣቶች መብታቸውን ሲጠይቁ ሰላማዊ መንገድና ሕግና ስርዓት በመከተል ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት አዎንታው አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በመጣው ለውጥ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አውስተው ወጣቱ ታግሎና መስዋዕትነት ከፍሎ የመጣው ለውጥ በጥፋት ኃይሎች መንገዱን እንዳይስት መጠበቅና የለውጡ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ በስልጠናው አገርና ዓለም አቀፍ ልምዶችን ያካተቱ ጽሁፎች ለውይይት መቅረባቸውን ጠቁመዋል።   

የህወሓት ዒ-ሕገ መንግስታዊ እንቅስቃሴና የፌዴራል ሥርዓቱን ለማዳን እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን የተመለከቱ  ጽሁፎችም እንዲሁ።

"ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የወጣቶች ትግል በብዝሃንት ላይ ለተመሰረተ አገራዊ አንድነት ግንባታ" በሚል ርዕስ የቀረበው ጽሁፍ በዋናነት ወጣቶች ላይ ያተኮረ መሆኑንም አክለዋል።

ይህም "ወጣቶች ሕገ መንግሥቱን፣ የፌዴራል ሥርዓቱንና አገራቸውን የተመለከቱ ጉዳዮችን አውቀው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ያለመ ነው" ብለዋል።

ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔር ብሔረሶቦች ቀን የማጠቃለያ በዓል በአዲስ አበባ እንደሚከበርም አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ አስታውቀዋል።

በዓሉን የብሔረሰቦችን ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክና ቅርስ ከማስተዋወቅ ባለፈ ትስስራቸውንና ህብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን በሚያጠናክሩ ሥራዎች ለማክበር መታቀዱንም አብራርተዋል።

"በዓሉ ሕገ መንግሥቱንና የፌዴራል ሥርዓቱን ለማስተማርና ለማስረፅ የምንጠቀምበት መልካም አጋጣም ነው" ሲሉም ነው የገለጹት።

ከብሔር ብሔረሶቦች በዓል ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡ የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ወጣቱን በአገረ መንግስት ግንባታ ለማሳተፍ መድረኩ መዘጋጀቱ የሚበረታታ እንደሆነ ተናግረዋል።

የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ዕቅዶች በመንደፍ መንቀሳቀስ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ወጣቶች አገራቸውን ማወቅና በአገረ መንግሥት ግንባታ በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል።

በመድረኩ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የዲፕሎማሲና የውጭ ጉዳይ አማካሪ አቶ ሌንጮ ባቲ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም እና የሕገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኃይለየሱስ ታዬ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም