ቀጥታ፡

የአሮጌው ብር ኖት የቅያሬ ጊዜ ታህሳስ 6 ቀን ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ ህዳር 10/2013 (ኢዜአ) የአሮጌው ብር ኖት ቅያሬ ታህሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

ከያዝነው ወር ህዳር 22 ጀምሮ ደግሞ በአሮጌው የብር ኖት ግብይት መፈጸም የማይቻል መሆኑን አስታውቋል። 

ከመስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም አሮጌ የብር ኖቶች በአዲስ የብር ኖቶች እየተቀየሩ መሆኑ ይታወቃል።

የብር ኖት ቅያሬው በሶስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ መወሰኑም ይታወሳል።

በመሆኑም የአሮጌው የብር ኖት ቅያሬ ታህሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም የሚጠናቀቅ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ከዚህ ቀን በኋላ በባንኮች አሮጌ የብር ኖት እንደማይኖርም ገልጿል።

በዚሁ መሰረት የተፈቀደው የብር መቀየሪያ የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ 25 ቀናት ብቻ እንደቀሩት ይፋ አድርጓል።

ከህዳር 22 እስከ ታህሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ባሉት 15 ቀናት በአሮጌው የብር ኖት ግብይት መፈጸም መከልከሉንና ግብይቱን ማድረግ የሚቻለው በአዲሱ የብር ኖት መሆኑን አመልክቷል።

በመጨረሻዎቹ 15 ቀናት ማንኛውም ሰው አሮጌውን ብር ወደ ባንክ ሄዶ መቀየር እንደሚችል ነው ባንኩ የጠቆመው።

እስካሁን ያለው የብር መቀየሩ ሂደት በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቋል።

የፌደራል፣ የክልል፣ የከተማ አስተዳደሮችና የጸጥታ አካላት በቀሩት ቀናት ለሚካሄደው የአሮጌው የብር ኖት ቅያሬ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ባንኩ ጥሪውን አቅርቧል።

ከ100 ሺህ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ያለው የአሮጌው የብር ኖት ቅያሬ ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም መጠናቀቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም