ለታላቁ ህዳሴ ግድብና ለአካባቢው ደህንነት መረጋገጥ አስፈላጊው ጥበቃ ይደረጋል---የ22ኛ ክፍለ ጦር አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ ህዳሴ ግድብና ለአካባቢው ደህንነት መረጋገጥ አስፈላጊው ጥበቃ ይደረጋል---የ22ኛ ክፍለ ጦር አባላት
አሶሳ ህዳር 10/2013 (ኢዜአ) በሀገር መከላከያ የምዕራብ እዝ 22ኛ ንስር ክፍለ ጦር አባላት ሀገርንና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ እንደወትሮው በትጋት እየሰሩ መሆኑን ተናገሩ።
ከክፍለ ጦሩ አባላት መካከል ሌተና ኮረኔል ወንድሙ ሃብቴ እንደገለጹት የ22ኛ ንስር ክፍለ ጦር አባላት አብዛኞቹ ለ21 ዓመታት በትግራይ ክልል የህዝብ ደጀን በመሆን ማገልገላቸውን ተናግረዋል፡፡
“ሠራዊቱ የትግራይ ህዝብን ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ ሌት ተቀን በደሙ፣ በጉልበቱ፣ በገንዘቡ እና አቅሙ በቀፈቀደ ሁሉ መስዋዕትነት ከፍሏል” ብለዋል፡፡
ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን በሰሜን ዕዝ አባላት ላይ ያደረሰው ግፍ የተሞላበት ጭፍጨፋ ለሠራዊቱ ፈጽሞ የማይመጥን፣ አረመኒያዊ እና የሚወገዝ ድርጊት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የአብዛኛው የሰሜን ዕዝ ክፍለ ጦር አባላት በቅርቡ ለተጨማሪ ሀገራዊ ግዳጅ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንደተዛወሩ ገልጸው ለህዝብ ክብር የተሰዉ ጓዶቻቸውን በማሰብ በቁጭት እየሠሩ መሆኑን ሌተና ከሎኔል ወንድሙ አስረድተዋል፡፡
በሀገራችን ሠላም ሲያሳጣ የኖረውን የህወሃት አሸባሪ ቡድን በህግ ለማስገዛት የጀመርነውን ዘመቻ በቅርቡ በአሸናፊነት እንወጣለን ያሉት ደግሞ የክፍለ ጦሩ አባል ምክትል አስር አለቃ ገነት ቢቂላ ናቸው፡፡
የህዳሴው ግድብ ከፍጻሜ እስኪደርስ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን የገለጹት የሠራዊቱ አባል “በፕሮጀክቱ ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚነሳ የትኛውንም ሃይል አንታገስም” ብላለች።
የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ አካል ነው የሚሉት ምክትል አስር አለቃ ገነት “የጁንታውን ህወሃት አባላት አጋልጦ በመስጠት ለሠራዊቱ ያለውን አጋርነት ሊያሳይ ይገባል”ብለዋል ።
“የሰሜን ዕዝ አባሎቻችን መስዋዕትነት ተጨማሪ ወኔ እና ጉልበት ሆኖናል” ያለው ደግሞ ሻምበል ሄኖክ ተክለማርያም ነው።
“የጁንታው ተላላኪዎች በመተከል ዞን የግድቡን አካባቢ ለማወክ የሚያደርጉትን ጥረት በማክሸፍ ላይ እንገኛለን” የሚለው ሻምበል ሄኖክ ተላላኪዎችን ለህግ ለማቅረብ ሌት ከቀን እየሰራን ነው ሲል አስረድቷል፡፡
“ህዝባችን የሠጠን ህገ-መንግስቱን የመጠበቅ ሃላፊነት በመወጣት ሀገራችንን የማስከበር ተልዕኳችንን እናሳካለን” ብሏል ሻምበል ሄኖክ፡፡
ሠራዊቱ እየወሰደው በሚገኘው ህግን የመስከበር ዘመቻ የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ሠላሙ የሚመለስት ጊዜ ቅርብ እንደሆነም ተናግሯል፡፡
በምዕራብ ዕዝ የ22ኛ ንስር ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ነገሪ ቶሊና “ህብረተሰቡ ለሠራዊቱ ያሳየው ክብር ለበለጠ ሃላፊነት አነሳስቶናል” ብለዋል፡፡
ሠራዊቱ የህዝብ ልጅ ነው የሚሉት ብርጋዴር ጀኔራል ነገሪ ህዝብ ያለሀገር ሀገር ያለ ህዝብ አይኖርም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
“ከሰሜን ዕዝ አባላት ላይ የጁንታው ቡድን ተላላኪዎች በሆኑ ጥቂት ከሃዲዎች የተፈጸመው ዘግናኝ ጥቃት ክፉኛ አሳዝኖኛል” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
“በሠራዊቱ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ውስጣዊ አንድነታችንን ለማፈራረስ በተነሱ በድኖች የተጠነሰሰ ሴራ ነው” ያሉት ብርጋዴር ጀኔራል ነገሪ ሠራዊቱ ህዝባዊ ወገንተኝትን ያነገበ በመሆኑ ሴራው መክሸፉን ገልጸዋል፡፡
“ችግርን ተቋቁሞ ከማለፍ ባሻገር እንዴት ወደ ድል እንደሚቀየር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠንቅቆ ያውቃልም” ብለዋል፡፡
“የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ህዝብ ህልውና ነው” የሚሉት ብርጋዴር ጀኔራል ነገሪ ለፕሮጀክቱ ከገንዝብ ጀምሮ መስዋዕትነት ያልከፈለ ዜጋ እንደሌለ ገልጸው “ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ከምንጊዜውም በላይ ለዓለም አጉልቶ ያሳያ ነውም” ብለዋል ጀነራሉ፡፡
በጁንታው ተልዕኮ በህዳሴ ግድብ አካባቢው ሁከት ለመፍጠር የሚደረግ ተደጋጋሚ ሙከራ እንዳለ የሚገልጹት አዛዡ ሠራዊቱ ከውስጥም ሆነ ከውጪ ሊቃጡ ለሚችሉ ማናቸውም የጥፋት ድርጊቶች አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዘወትር በተጠንቀቅ እንደሚጠብቅ አስታውቀዋል፡፡
የምዕራብ እዝ ሠራዊት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝብ እንዲሁም ከክልሉ ልዩ ሃይል እና ከኢትዮጵያ አየር ሃይል ጋር ጠንካራ ቅንጅት በመፍጠር እየሰራ መሆኑን ብርጋዴር ጀኔራል ነገሪ አብራርተዋል።