ቀጥታ፡

የትግራይ ህዝብ ሀገር ወዳድና ሰላም ፈላጊ እንጂ ከህወሃት ቡድን ጋር አንድ ነው ማለት ፍፁም ስህተት ነው-- የትግራይ ተወላጆች

አዲስ አበባ ህዳር 10/2013 (ኢዜአ) የትግራይ ህዝብ ሀገር ወዳድና ሰላም ፈላጊ እንጂ ከህወሃት የጥፋት ቡድን ጋር አንድ ነው ማለት ፍፁም ስህተት መሆኑን በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱም የኢትዮጵያ ጀግኖች ጠብቀው ዛሬ ላይ ያደረሷትን አገር በጥቂቶች ሴራ አትፈርስም እንታገላቸዋልንም ብለዋል።

በቅርቡ በትግራይ ክልል በነበረው የሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመው አስነዋሪ ድርጊትም የትግራይ ህዝብን የማይወክል የከሃዲዎች ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የትግራይ ህዝብና ህወሃትን አንድ ናቸው በማለት አንዳንዶች ከጥፋት ሃይል ጋር መፈረጃቸውም ተገቢነት የሌለውና ሰላም ወዳዱ የትግራይ ህዝብ እንደማይቀበለው አረጋግጠዋል።

አገሪቱን ሊያጠፉና ሊያፈራርሱ የሚተጉ ጥቂት ቡድኖች መኖራቸውን የጠቀሱት ነዋሪዎቹ የትግራይ ህዝብ የሚያወግዛቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ፕሬዘደንት ወይዘሮ መላኬ አለማየሁ እንዳሉትም በህወሃት እጥፊ ቡድን የሚሰራጨው ወሬ መሰረት የሌለው መሆኑን አብራርተዋል።

ጁንታው "የትግራይ ህዝብ ልትወረር ነው፣ ትግራይን ሊያጠፏት ነው" የሚሉ የሃሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በማሰራጨት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የጥፋት ቡድኑ ህጻናት ልጆችን ለውጊያ በማዘጋጀት "እናንተ ሞታችሁ እኔ ልኑር" የሚል ስግብግብ ጁንታ መሆኑን አብራርተዋል።

አሁን ላይ መንግስት እያከናወነ ያለው ህግ የማስከበር እርምጃው በክልሉ የመሸገውን ጁንታ ለህግ የማቅረብ እንጂ አገር ወዳዱን የትግራይ ህዝብ የሚመለከት እንዳልሆነ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም