ቀጥታ፡

ስድስተኛው አገር አቀፍ የቱሪዝምና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንት በአዲስ አበባ ተጀመረ

አዲስ አበባ ግንቦት 5/2010 ስድስተኛው አገር አቀፍ የቱሪዝምና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንት ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀመረ። ዘንድሮ የሚከበረው ስድስተኛው የቱሪዝምና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንት 'ሰላም ለቱሪዝም፤ ዘላቂ የቱሪዝም  ልማት ለሕዳሴያችን' በሚል መሪ ሐሳብ ነው በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ያለው። የቱሪዝም ዘርፉን የሚገልጹ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ በዘርፉ ስልጠና የሚሰጡ ዩኒቨርስቲዎች፣ ከውጪ አገራት በቱሪዝም ዘርፍ ጥሩ ተሞክሮ ያላት የኬንያ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ ሌሎች አውደ ርእይ ያቀርባሉ ። በዘርፉ ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናትና ምርምሮች ይቀርባሉ ፤ የስፖርትና የአገር ቱሪዝምን የሚያነቃቃ የተራራ ላይ ሩጫ ውድድርም ይካሄዳል። በተመሳሳይ በቱሪዝም ሳምንቱ በአዲስ አበባ የስነ ጽሑፍ፣ የቀለም ቅብ፣ የስእልና ሌሎች ዘርፉን የሚገልጹ ውድድሮች ይካሄዳሉ ነው የተባለው። የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዳሬክተር አቶ አሸብር ተክሌ በዚሁ ጊዜ የቱሪዝም ዘርፉ የአገር ገጽታን ለመገንባትና ኢኮኖሚን ለማሳደግ ያለው ሚና ጉልሕ ነው ብለዋል። በመሆኑም አሁን ላይ እየጨመረ የመጣውን የጎብኝዎች ፍላጎት ማሟላት ይቻል ዘንድ በእውቀት የተካነና ተወዳዳሪ የቱሪዝም ባለሙያ ማፍራትና ማነቃቃት  አስፈላጊ ነው ይላሉ። "የቱሪዝም ዘርፉ በቅርቡ በመንግስት በኩል ልዩ ትኩረት አግኝቷል" የሚሉት አቶ አሸብር፤ አገሪቷ ካላት እምቅ ሀብት፣ የቱሪዝም እድልና ፍላጎት አንጻር በርካታ መሰራት ያለባቸው ተግባራት እንዳሉ ይገልጻሉ። የሆቴሎች ደረጃ፣ ብዛትና ስርጭት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና ጥራት፣ በዘርፉ የተሰማራው የሰለጠነ የሰው ኃይል ብዛትና ብቃት አንዲሁም ሌሎች የዘርፉ ችግሮች ሁሉ ትኩረትና ፈጣን ምላሽ የሚሹ ናቸው ብለዋል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና በቀጣይ የቱሪዝም ዘርፉ የሚጠበቅበትን እንዲያበረክት አውደ ርእዩና የእንግዳ ተቀባይነት ሳምንቱ የተሻለ እድል እንደሚፈጥርም እምነታቻውን ገልጸዋል። በቅርቡ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ወይዘሮ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው "የበርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ባሕላዊ እሴት ባለቤት የሆነችው አገራችን በአየር ንብረት መለዋወጥና በሰላም እጦት ምክንያት ሀብቶቿን በሚፈለገው መጠን እንዳትጠቀም አድርጓታል" ብለዋል። በዚህም ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ዘርፉ ለማሳከት ያቀደውን እውን ማድረግ እንዳልቻለ ገልጸዋል። በመሆኑም በቅርብ የታየውን ሰላምና መረጋጋት ለማስቀጠል ሁሉም ሕብረተሰብ የግሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል። የቱሪዝምና የእንግዳ ተቀባይነት ሳምንቱ መነቃቃትና ግንዛቤን ለሕብረተሰቡ የመፍጠር አቅም እንዳለውም ወይዘሮ ፎዚያ ገልጸዋል። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 9 ድረስ የሚካሄደውን ስድስተኛው አገር አቀፍ የቱሪዝምና የእንግዳ ተቀባይነት ሳምንት ያዘጋጀው የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ሲሆን ተቋሙ ከ1961ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 49 ዓመታት እየሰራ ያለ አንጋፋ የሙያ ስልጠና ተቋም ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም