ለሃያ ዓመታት ተቋርጦ የነበረው በረራ በዛሬው እለት ይጀምራል

79
አዲስ አበባ ሃምሌ 11/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሃያ ዓመታት የተቋረጠውን የአስመራ በረራ በዛሬው እለት ይጀምራል። ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ 465 ሰዎችን የያዘ የንግድ በረራ ዛሬ ወደ አስመራ ያቀናል። አስመራ ከሚሄዱት የህዝብ ለህዝብ ቡድኑ መካከል የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ  ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ባለሀብቶችና ለዓመታት ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተው በኢትዮጵያ ሲኖሩ የነበሩ ኤርትራውያን ይገኙበታል ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በኤርትራ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ የአየር ትራንስፖርት እና ሌሎች አገልግሎቶች በሁለቱ ሀገራት መካከል እንደሚጀር ከስምምነት ተደርሶ ነበር። ከስምምነቱ ውስጥም ወደብን በጋራ መጠቀም፣ ኤምባሲዎቻቸውን መልሶ መክፈት፣ የአየር ትራንስፖርትና ሀገራቱ በስልክ እንዲገናኙ  የሚሉት ይገኙበታል። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ በዛሬው እለት በይፋ የሚጀምር ይሆናል። ኤርትራ የአዲስ አበባ ኤምባሲዋን መልሳ መክፈቷ የሚታወስ ሲሆን ኢትዮጵያም ኤምባሲዋን በአስመራ ለመክፈት ዝግጅት ላይ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ሲመጣም ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር ሳይገናኙ የቆዩ በርካታ ኤርትራውያንን ይዞ እንደሚመጣም ታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም