ቀጥታ፡

የስልጤ ዞን ነዋሪዎች ለአገር መከላከያ ሠራዊት 159 ሠንጋዎችን እና 5 ነጥብ 1 ሚልዮን ብር ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 9/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ነዋሪዎች ለአገር መከላከያ ሠራዊት 159 ሠንጋዎች እና 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ፡፡

ከስለጤ ዞን የተወከሉ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የዞኑ የመንግስት ሃላፊዎች የነዋሪዎችን ድጋፍ ዛሬ በምድር ኃይል ግቢ ተገኝተው አስረክበዋል፡፡

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር በርክክቡ ወቅት እንዳሉት፤ የዞኑ ነዋሪዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ለመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፍ አድርገዋል።

በአጠቃላይም አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ነዋሪው ድጋፍ ያደረገው ከ10 ነጥብ 1 ሚልዮን ብር በላይ ግምት ያለው መሆኑንም ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡

ነዋሪው በቀጣይ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል፡፡

ከስልጤ ዞን የተወከሉት የሃይማኖት አባት ሃጂ መሃመድ ከሊል ህገ ወጥ ቡድኑ በአገር መከላከያ ላይ በፈጸመው ድርጊት የዞኑ ህዝብ ማዘኑን ገልጸዋል፡፡

ድርጊቱን በፈጸመው የህወሃት ቡድን ላይ የተጀመረው የህግ ማስከበር ዘመቻ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የስልጤ ህዝብ የሚችለውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

የስልጤ የሃገር ሽማግሌ ሼህ አብዱረሃማን ሼህዋጁ በበኩላቸው “ሰላማዊ ለሆነ መንግስት እና የመከላከያ ሰራዊት ክህደት አይገባውም ነበር” ብለዋል፡፡

የስልጤን ዞን ያደረገውን ድጋፍ የተቀበሉት የመከላከያ የሚኒስትር ዴኤታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሲሳይ ለተደረገው ስጦታ አመስግነዋል።

በተመሳሳይ የኢሉ አባቦራ ዞን የአሊ ዞን ነዋሪዎችም ለመከላከያ ሰራዊቱ 22 በሬዎችን ድጋፍ አድረገዋል፡፡

በተወካዮቻቸው በኩል በምድር ኃይል ቅጥር ግቢ ተገኝተውም ድጋፉን አስረክበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም