የግብርና ምርታማነትና የመሬት አስተዳደር ስርዓትን የሚያሻሽል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ምርታማነትና የመሬት አስተዳደር ስርዓትን የሚያሻሽል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 9/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ግብርናና የመሬት አስተዳደር ስርዓትን ወደተሻለ ደረጃ ማድረስ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።
የፕሮጀክቱን ማስጀመሪያ የስምምነት ሰነድ ግብርና ሚኒስቴርና የጀርመን መንግስት ተፈራርመዋል።
ፕሮጀክቱ ግብርና ሚኒስቴር ከጀርመን መንግስትና ከአውሮፓ ኅብረት ባገኘው ድጋፍ ለአራት ዓመታት የሚተገብረው ነው።
የግብርና ሚኒስትር አማካሪ አቶ አበራ ሙላት እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የተሰራበትና የሁለተኛ ምዕራፍ ትግበራ ነው።
ፕሮጀክቱ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀምን በተመለከተ በባለሃብቶች የሚለሙ መሬቶችን ከአነስተኛ አርሶ አደሮች ጋር በትብብር በማልማት ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
“ከቤኒሻንጉል ጉሙዝና ከጋምቤላ ክልሎች በተገኘው ተሞክሮ ፕሮጀክቱ በመሬት አጠቃቀም በርካታ ለውጦችን ያሳየ በመሆኑ ይህንኑ ውጤት ተኮር ተግባር ለማስፋት ይሰራል” ብለዋል።
በሁለተኛው ዙር የፕሮጀክቱ ትግበራ የአማራ ክልል የሚካተት ሲሆን በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በጋምቤላ ክልሎች የተጀመረውም ይቀጥላል።
በኢትዮጵያ የጀርመን የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስቴር ተጠሪ ሚስ ላውራ ሸሚት ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያዊያን የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ ሚስተር ዶሚኒክ ዳቮክስ ድጋፉ የተደረገው የኢትዮጵያ ግብርና ምርታማነትና የመሬት አጠቃቀም እንዲሻሻል ለማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል።