ቻይናና ፈረንሳይ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን ተረድተዋል - በአገራቱ የሚገኙ አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ቻይናና ፈረንሳይ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን ተረድተዋል - በአገራቱ የሚገኙ አምባሳደሮች
አዲስ አበባ፣ ህዳር 9/2013 (ኢዜአ) የቻይናና ፈረንሳይ መንግስታት በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው የህግ ማስከበር ዘመቻ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እንደሆነ ግልጽ አቋም መያዛቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው በአገራቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ገለጹ።
የሕወሓት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል በሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ መንግስት የሕግ ማስከበርና አገርን የማዳን ተልዕኮ ለመከላከያ ሰራዊት ሰጥቶ ዘመቻ እየተካሄደ ይገኛል።
ኢዜአ መንግስት በትግራይ ክልል እየወሰደ ባለው የሕግ ማስከበር ዙሪያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ከማስረዳት አኳያ እየተከናወነ ያለውን ስራ በተመለከተ በቻይናና በፈረንሳይ የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችን አነጋግሯል።
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የሕግ ማስከበር እርምጃ ገለጻ የሚያደርግና ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎችን የሚያከናውን ጊዜያዊ ግብረ ሃይል ኤምባሲው ማቋቋሙን ገልጸዋል።
“በቤጂንግ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲሁም በሻንጋይ፣ ቾንግቺንግ በጉዋንዡ ከተሞች ባሉት የቆንስላ ጽህፈት ቤቶች የሚገኙ ዲፕሎማቶችና ሰራተኞች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው” ብለዋል።
ለቻይና መንግስት፣ ለቻይና ባለሀብቶች፣ በቻይና ለሚገኙ ለምስራቅ አፍሪካ አገሮች እንዲሁም በቻይና ለሚኖሩ የተወሰኑ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎችና ተማሪዎች ማብራሪያ መሰጠቱን አመልክተዋል።
ሕግ ማስከበሩ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እንደሆነና የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንደማያስፈልገው ለቻይና መንግስት ገለጻ መደረጉን ጠቅሰዋል።
መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያፈሱ ባለሀብቶች እንዲሁም በስራቸው ለሚገኙ ሰራተኞችና መሰረተ ልማቶች ጥበቃ እየተደረገ እንደሆነና የተመረጡ ኢላማዎች ላይ ብቻ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ባለሀብቶቹ እንዲረዱት መደረጉን አመልክተዋል።
በቻይና የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎችና ተማሪዎች እየተካሄደ ስላለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ግልጽ የሆነ መረጃ እንዲያገኙ መደረጉን አምባሳደር ተሾመ ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያኑ ለመከላከያ ሰራዊቱ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የተቋቋመው ግብረ ሃይል በቻይና ብዙሃን መገናኛዎች በመቅረብ በወቅታዊ ሁኔታው ላይ ማብራሪያ በመስጠት፣ ብዙሃን መገናኛዎቹ የሚያስተላልፏቸውን መረጃዎች መከታተልና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ትክክለኛ መረጃዎችን ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተከናወነ እንደሆነም ተናግረዋል።
በፈረንሳይ፣ ስፔንና ፖርቹጋል የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ በበኩላቸው የሕግ ማስከበር ዘመቻውን በተመለከተ ለፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለፈረንሳይ ፓርላማ አባላትና ለሌሎች የስራ አስፈጻሚ አካላት ማብራሪያ መሰጠቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በፈረንሳይ ለሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ብዙሃን መገናኛዎች እንዲሁም ኤምባሲው በሚሸፍናቸው አገሮች ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገለጻ መደረጉን አመልክተዋል።
የፈረንሳይ መንግስት የዘመቻውን ይዘትና አላማ እና በሕወሓት ቡድን በኩል የሕግ ማስከበር ስራው ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው እያደረገ ያለውን ጥረት በግልጽ መረዳቱን ተናግረዋል።
በፈረንሳይ፣ ስፔንና ፖርቹጋል የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የአገር መከላከያ ሰራዊቱን ለመደገፍ ቆርጠው መነሳታቸውንና ለሰራዊቱ የሀብት ማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።