ኢትዮጵያን አሜሪካንስ ሲቪክ ምክር ቤት የሕወሃትን ወንጀል ለዓለም ማህበረሰብ በማሳወቅ ላይ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን አሜሪካንስ ሲቪክ ምክር ቤት የሕወሃትን ወንጀል ለዓለም ማህበረሰብ በማሳወቅ ላይ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 9/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን አሜሪካንስ ሲቪክ ምክር ቤት የሕወሃት ቡድን የሚሰራውን ወንጀል ለዓለም ማህበረሰብ የማሳወቅ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።
በትውልደ ኢትዮጵያውያን የተመሰረተው ኢትዮጵያን አሜሪካንስ ሲቪክ ምክር ቤት መስራችና አስተባባሪ ኢንጂነር ዐይንእሸት ገላጋይ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ህወሃት በአገር መከላከያ ሃይል የሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን ክህደት አውግዘዋል።
ከዚህ በፊትም ሕወሃት በኢትዮጵያዊያን ላይ በፈጸመው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂ እንዲሆን ኤችአር 128 የመፍትሔ ሃሳብን ለአሜሪካ መንግስት ማቅረቡን አስታውሰዋል።
የሕወሃት ቡደን አሁንም በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ዘር ተኮር ጥቃት በመፈፀም የእርስ በርስ እልቂት እንዲፈጠር እየሰራ ስለመሆኑ አረጋግጠናል ብለዋል።
ህወሃት በአገር ጠባቂ ሃይል ላይ ጥቃት በመፈፀም በአገር ሉዓላዊነት ላይ አደጋ መደቀኑን ጠቅሰው ድርጊቱን በዝምታ ማለፍ አይቻልም ብለዋል።
በመሆኑም ምክር ቤቱ በተለያዩ የዓለም አገራት ከሚገኙ የኢትዮጵያ ማህብረሰብ አደረጃጀት ጋር በመቀናጀት የህወሃትን እኩይ ተግባርና መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቅ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ሕወሃት በአገር ሉዓላዊነት ዘብ በቆመ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን የክህደት ወንጀል ጨምሮ በመላ አገሪቱ ኢትዮጵያን ለማተራመስ እንደሚሰራ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቅ ስራ እያከናወነ ነው።
ሕወሃት በሰሜን እዝ ላይ የፈፀመውን ደባ የሚያስረዳ ዝርዝር መረጃ ለአሜሪካ መንግስት፣ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዲሁም ለሌሎች አህጉር አቀፍ ድርጅቶች የማሳወቅ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በቀጣይም የከሃዲው ቡድን ወንጀል ፈፃሚዎች በህግ እንዲጠየቁ ምክር ቤቱ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዚህ ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች የአገር ክህደት ወንጀል መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ የዳያስፖራው ማህበረሰብ የኢትዮጵያዊያን ድምጽ በመሆን ከመንግስት ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል።።