ህወሓት ሃገር ጠል የሆነ የባንዳ ስብስብ መሆኑን የቀድሞ የሠራዊት አባላት ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ህወሓት ሃገር ጠል የሆነ የባንዳ ስብስብ መሆኑን የቀድሞ የሠራዊት አባላት ገለጹ
ደብረ ብርሃን፣ ህዳር 9/2013(ኢዜአ) ህወሓት የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊትን በመድፈር ባንዳነቱን ያሳየ ሃገር ጠልና የከሀዲ ስብስብ መሆኑን በደብረ ብርሃን ከተማ የሚኖሩ የቀድሞ ጦር ሠራዊት አባላት ገለጹ።
ከአባላቱ መካከል ወታደር ደጀኔ ግዛው ለኢዜአ እንዳሉት ህወሓት ከጥንስሱ ሲፈጠር ከሃዲና የሌባ ስብስብ ነው።
መከላከያ ሠራዊቱ ለራሱና ቤተሰቦቹ ሳይኖር ለሃገርና ህዝብ ሲል ህይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ የቁርጥ ቀን ጋሻ ነው፤ ይህን ሃይል መድፈር ኢትዮጰያውያንን ለባዕድ አሳልፎ መስጠት ነው ብለዋል።
ይህ ሀገር ጠልና ከሀዲ ቡድን በፈፀመው ወንጀል ልክ በህግ ተጠያቂ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ አመልክተው የትግራይ ህዝብ ፣የልዩ ሃይልና የሚሊሻ አባላትም የህወሃትን የሴራ ፖለቲካ በመረዳት ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጎን በመሆን ጁንታውን ሊታገል እንደሚገባ ገልጸዋል።
ወታደር ይታገሱ ኃይለማሪያም በበኩላቸው የህወሃት የጥፋት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው ክህደት ሊታሰብ የማይቻል እና ታሪክ የማይዘነጋው አሳዛኝ ድርጊት ነው ብለዋል።
ሀገር ከትውልድ ወደ ትውልድ የምትሸጋገር እንደሆነች ጠቅሰው፤ ታሪክን ያበላሸውንና ሃገር አፍራሹን ጁንታ ሙሉ በሙሉ ለህግ ማቅረብ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።
በራስ ወገን ላይ እንዲህ ዓይነት ሰይጣናዊ ተግባር መፈጸም የሚያሳፍር መሆኑን ወጣቶች በመገንዘብ መንግስት የጀመረው ህግ የማስከበር ስራ ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
''የሀገር ኩራት በሆነው መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈፀመው ጥቃት በውጭ ጠላት ያልተደረገና የማይጠበቅ የባንዳነት ተግባር ነው'' ብለዋል።
በህወሃት የጥፋት ቡድን የተሸረሸረውን የሃገር አንድነት መልሶ ለመገንባት ወጣቱ በጋራ መቆምና ይህን ቡድን ማጥፋት ይገባል ያሉት ደግሞ መጋቢ ሀምሳ አለቃ ሐብታሙ ደምሴ ናቸው።
ሀገር ጠል የሆነው ህወሓት በህዝቦች መካከል ጥላቻና ጥርጣሬ እንዲኖር የተዛባ ትርክት በመፍጠር ህዝብን ሲከፋፈል የነበረ ከሀዲና ባንዳ ነው ብለዋል።
ይህንን የጥፋት ቡድን ሥርዓት ለማሲያዝ በሃገር መከላከያ ሠራዊት የተጀመረው ህግን የማስከበር ስራም መጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።
ጊዜው ያለፈበት የእንደራደር ጥያቄ በማንኘውም መለኪያ ተቀባይነት የሌለውና ወንጀለኛን ከህግ የሚያርቅ በመሆኑ ሊታሰብም እንደማይገባም ተናግረዋል።
ህግን ለማስከበር መንግስት በከሃዲው ቡድን ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ በመደገፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አባላቱ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።