በተገቢው መንገድ ባለ መወሰዳቸው ፈዋሽነታቸው የቀነሰ መድሃኒቶች እየተበራከቱ ነው - ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በተገቢው መንገድ ባለ መወሰዳቸው ፈዋሽነታቸው የቀነሰ መድሃኒቶች እየተበራከቱ ነው - ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ህዳር 9 /2013(ኢዜአ) በተገቢው መንገድ ባለ መወሰዳቸው ምክንያት በሽታን የተላመዱና ፈዋሽነታቸው የቀነሱ መድሃኒቶች መበራከታቸውን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች ጀርሞችን በመላመዳቸው በሚከሰት የጤና ችግር በዓመት ከ750 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚሞቱ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች ግንዛቤ ማስጨበጫ ሣምንትን አስመልክቶ ጤና ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች በሽታ አምጪ ተህዋሲያንን በቀላሉ በመላመዳቸው ፈዋሽነታቸው እየቀነሰ መሆኑን አስታውቋል።
መግለጫውን የጤናና የግብርና ሚኒስቴሮች እንዲሁም የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በጋራ የሰጡ ሲሆን በጤና ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ ሰማን በኢትዮጵያ ወረርሽኝን ጨምሮ በርካታ ተላላፊና በቀላሉ የሚዛመቱ የበሽታ አይነቶች በየወቅቱ እንደሚከሰቱ ገልፀዋል።
እነዚህን በሽታዎች የሚያክሙና የሚፈውሱ መድሃኒቶች በስራ ላይ መኖራቸውንም ተናግረው አብዛኛዎቹ የበሽታ አይነቶች ቢታከሙም ታማሚው ግለሰብ አልያም ማኅበረሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ካላደረገ የማገርሸት ሰፊ ዕድል እንዳላቸው አስታውቀዋል።
በዚህ የተነሳ ያለአግባብ የሚወሰዱ፤ በሽታዎችን የተላመዱና ፈዋሽነታቸው የቀነሱ መድሃኒቶች እየተበራከቱ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ያዕቆብ ገለጻ ኮቪድ-19 ከፍተኛ ስጋት በሆነበት በዚህ ወቅት ሰዎች ሕመም ሲሰማቸው ወደ ጤና ተቋም ከመሄድ ይልቅ የጸረ ተህዋሲያን መድሃኒቶችን ያለ ጤና ባለሙያ ምክር የመጠቀም ፍላጎት ማሳየታቸውን ጥናቶች ያሳያሉ።
በኢትዮጵያ 80 በመቶ የሚሆነው መድሃኒት ከውጭ የሚገባና የተለያዩ አገራት ምርት መሆኑ ደግሞ ለችግሩ ተጨማሪ መንስኤ መሆኑን ጠቁመዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ተህዋሲያን እያደጉ ያሉ አገራትን በስፋት እያጠቁ ይገኛሉ ብለዋል።
ተህዋሲያኑን ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ካልቀጠለ በዕጽዋትና በእንስሳት ላይ ከሚደርሰው ጉዳት ባሻገር ማኅበራዊ ጫናውም ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመው ይህን በመገንዘብ በጉዳዩ ላይ በሚካሄዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮች ሁሉም አካላት ተሳትፎ በማድረግ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአደገኛና ደረቅ ቆሻሻ ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ግርማ ገመቹ በበኩላቸው በቅርቡ የወባ ትንኝ በሚገኝባቸው አካባቢዎች የፀረ ወባ ርጭት መካሄዱን አስታውሰው የወባ ትንኟ ኬሚካሉን በመላመዷ ማጥፋት እንዳልተቻለ ገልፀዋል።
በመሆኑም ለዚሁ ዓላማ ተከማችቶ የነበረው ከ1 ሺህ 400 ቶን በላይ ኬሚካል ምንም አይነት ጥቅም ሊሰጥ እንደማይችል ነው የጠቆሙት።
ኬሚካሉ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ እየተወገደ መሆኑንና ይህም በኢኮኖሚ ላይ እያስከተለ ያለውን ጫና ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች ግንዛቤ ማስጨበጫ ሣምንት "ክብካቤ ለፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች" በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ ለ5ኛ፤ በዓለም ደግሞ ለ6ኛ ጊዜ እስከ ህዳር 15 ይከበራል።