ሰራዊቱ እያካሄደ ባለው የህግ ማስከበር እና የአገር ህልውና ዘመቻ ድል እየተጎናጸፈ ነው- ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
ሰራዊቱ እያካሄደ ባለው የህግ ማስከበር እና የአገር ህልውና ዘመቻ ድል እየተጎናጸፈ ነው- ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 9/2013 (ኢዜአ) ሰራዊቱ እያካሄደ ባለው የህግ ማስከበር እና የአገር ህልውና ዘመቻ ድል እየተጎናጸፈ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
የህወሃት ጁንታ አብያተ ክርስቲያናትን ለጦር ማከማቻና ማዘዣነት እያዋለ ስለመሆኑም ደርሰንበታል ብለዋል።
የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ሕግ የማስከበር እርምጃ ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በምዕራብ ግምባር የጀመረው የሰራዊቱ እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከዳንሻ ተነስቶ ባአከርን፣ ማይከድርን ተቆጣጥሮ ቃፍታ ሁመራ መግባቱን ገልጸዋል።
በመቀጠልም በአዲ ጎሹ በኩል ሽራሮን ተቆጣጥሮ በአዲ ንብረድ፣ አዲ ጎዞሞን ተቆጣጥሯል ብለዋል።
በትናንትናው እለትም ሰራዊቱ ባደረገው ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሽሬን መቆጣጠሩን ገልጸዋል።
በደቡብ ግንባርም ዋጃና አላማጣን ተቆጣጥሮ፤ በምስራቅ በኩልም በጨርጨር አድርጎ መሆኒ ደርሷል ነው ያሉት።
የአገር መከላከያ ሰራዊት ራያ ቆቦን ከጁንታው ታጣቂ ሃይል ነጻ ያወጣ መሆኑን ገልጸው ራያ አዘቦ ጥቂት ቦታዎች እንደሚቀሩ አብራርተዋል።
እስካሁን በተደረጉት የሕግ ማስከበር እርምጃዎች ሰራዊቱ በደረሰበት ቦታ ሁሉ የትግራይ ሕዝብ በደስታ እየተቀበለው መሆኑንም ገልጸዋል።
የህወሃት ጁንታ "ለውጊያ" በሚል ህዝቡን ቀደም ብሎ አስታጥቆ የነበረ ቢሆንም የአገር መከላከያ ሰራዊት በየደረሰበት ሁሉ ህዝቡ ለሰራዊቱ ትጥቁን እያስረከበ መሆኑን ገልጸዋል።
በሽሬ መስመር ብቻ ሕዝቡ 200 መትረየሶችን ለሰራዊቱ ማስረከቡን ጠቅሰዋል።
ህዝቡ ጽንፈኛ ቡድኑ የደበቃቸውን መሳሪያዎች በማጋለጥ ረገድም ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
የህወሃት ጁንታ የክልሉን ልዩ ሃይልና ሚሊሻ በማደናገር ለውጊያ ማሰለፉን የገለጹት ጀነራል ብርሃኑ በርካቶች በሰላም ለሰራዊቱ እጃቸውን እየሰጡ ነው ብለዋል።
የህወሃት ጁንታ በመሸነፍ ላይ በመሆኑ ህዝብን ለመጉዳት የተለያዩ ጥፋቶችን በመፈፀም ላይ ሲሆን አብያተ ክርስቲያናትንም ለጦር ማከማቻና ማዘዣነት እያዋለ ስለመሆኑ ደርሰንበታል ብለዋል።
ድልድዮችን፣ መንገዶችንና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በማፍረስ የህዝብ ፀር መሆኑን እያሳየ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
የመከላከያ ሰራዊቱን እንቅስቃሴ ለመግታት ድልድዮችንና መንገዶችን በማፍረስ ቢሞክርም ሰራዊቱ ግን ወደ ፊት እየገሰገሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የጽንፈኛ ቡድኑ ሽንፈት እውን እየሆነ ሲመጣ አፈቀላጤዎቹ ሰራዊቱ በተለያዩ አገራት እንደተደገፈ አድርገው የሚያሰራጩት መረጃም ፍጹም ሀሰት ስለመሆኑ አብራርተዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ አስር ሺህ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊቶች በተለያዩ ሀገራት ተሰማርተው አሁንም ተልዕኳቸውን እየፈጸሙ ይገኛሉ።
በተጨማሪም በርካታ እጩ ሰራዊቶች በስልጠና ላይ መሆናቸውንም ጠቁመው፤ ህግ የማስከበር እርምጃው የተጠቀሱትን ሰራዊቶች ሳይጨምር እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
በጁንታው ሃይል ላይ ህግ የማስከበር እርምጃውን ለማጠናቀቅ በስፍራው ከተሰማራው ሰራዊት አቅም በላይ አለመሆኑንም ገልጸዋል።
የጽንፈኛ ቡድኑ ውሸትና ፕሮፓጋንዳ የለመደ በመሆኑ ህዝቡ ይገነዘባልም ብለዋል ኢታማዦር ሹሙ።