ቀጥታ፡

የተለያዩ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ለሰራዊቱ ደም ለገሱ

አዲስ አበባ ህዳር 9 / 2013(ኢዜአ) የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሰራተኞችና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሥራ አመራር አባላትና ሠራተኞች በህግ ማስከበር ዘመቻ በመሳተፍ ላይ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ልዩ ኃይል አባላት ደማቸውን ለግሰዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ሥር የሚገኙ 15 የመንግሥት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አመራሮችና ሰራተኞችም የገንዘብ ድጋፍና የደም ልገሳ አድርገዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፤ የተቋሙ ሰራተኞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ፍቅርና አብሮነት ለማሳየት ደማቸውን መለገሳቸውን ገልጸዋል።

 በቀጣይም ሰራዊቱን በሁለንተናዊ መልኩ ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ከሚኒስቴሩ ሰራተኞች መካከል ወይዘሮ ዮዲት በቀለ "ለአገራችን መከታ ለሆነው ሰራዊታችን ደማችንን ለግሰናል በቀጣይም ሌሎች ድጋፎችን እናደርጋለን" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ በህግ ማስከበርና የአገር ህልውና ዘመቻ ላይ ለተሳተፈው የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ከልል ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ደማቸውን በመለገሳቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የባንኩ አመራር አባላትና ሠራተኞች ከደም ልገሳ በተጨማሪ በቀጣይ ሁለንተናዊ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በዛሬው እለት ደማቸውን የለገሱት በአዲስ አበባ የሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፎች ሰራተኞች ሲሆኑ በመላ አገሪቱ የባንኩ ቅርንጫፎች እስከ ህዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም ልገሳውን እንደሚያደርጉ ታውቋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ሥር የሚገኙ 15 የመንግሥት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አመራሮችና ሰራተኞችም ደማቸውን በመለገስ ለሰራዊቱ አጋርነታቸውን አሳይተዋል። 

ከደም ልገሳው በተጨማሪ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ በማዋጣት ለሰራዊቱ ገቢ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም