የጋሞ ዞን ነዋሪዎች ለመከላከያ ሠራዊት 6 ሚሊዮን ብር እና 77 ሠንጋዎችን አበረከቱ - ኢዜአ አማርኛ
የጋሞ ዞን ነዋሪዎች ለመከላከያ ሠራዊት 6 ሚሊዮን ብር እና 77 ሠንጋዎችን አበረከቱ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 9/2013 (ኢዜአ) የደቡብ ክልል ጋሞ ዞን ነዋሪዎች ለአገር መከላከያ ሠራዊት 6 ሚሊዮን ብር እና 77 ሠንጋ በሬዎችን አበረከተ፡፡
የኢሉ አባቦራ ዞን ሦስት ወረዳዎች ነዋሪዎችም ለመከላከያ ሠራዊቱ 37 ሰንጋዎችን አበርክተዋል፡፡
ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የጋሞ አገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የነዋሪዎቹን ድጋፍ ዛሬ በምድር ኃይል ግቢ ተገኝተው አስረክበዋል፡፡
የዞኑ ነዋሪዎች ለመከላከያ ሠራዊቱ ያላቸውን አክብሮት ለመግለጽ 6 ሚሊዮን ብር፣ 77 ሰንጋ በሬዎች፣ 34 ፍየሎችና ሁለት አይሱዙ የጭነት መኪና ሙዝ ልከዋል።
መከላከያ ሠራዊቱ የጀመረው የሕግ ማስከበር ሥራ በድል እስከሚጠናቀቅ የዞኑ ነዋሪዎች ከጎኑ እንደሚቆሙ ማረጋገጣቸውንም ዋና አስተዳዳሪው ገልፀዋል፡፡
ከጋሞ የአገር ሽማግሌዎች የተወከሉት አቶ መንግስቱ ደምሴ ነዋሪዎቹ መንግስት እያደረገ ያለውን የሕግ ማስበከር ሥራ እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ለሕግ ቀርቦ ፍትህ እስኪረጋገጥ ድረስ የአካባቢያቸውን ሕዝብ ለድጋፍ በማነሳሳት ከመንግስትና ከመከላከያ ሠራዊት ጎን እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል።
ሊቀ ህሩይ ገሪማ ጌታነህም የሃይማኖት አባቶች ለአገር ሠላምና አንድነት ከመፀለይ ባሻገር የአካባቢያቸውን ሠላም መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በጋሞ ዞን ጸረ ሠላም ኃይሎች በእምነት ተቋማትም ይሁን በተለያዩ ቦታዎች የሕዝቡን ሠላም እንዳይረብሹ ምዕመናንን ከማስገንዘብ ጀምሮ አካባቢያቸውን ተግተው እየጠበቁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት በመከላከያ ሚኒስቴር የሚኒስትር ዴኤታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሲሳይ ለጋሞ ሕዝብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይ የኢሉ አባቦራ ዞን ሦስት ወረዳዎች ነዋሪዎች ለመከላከያ ሠራዊቱ 37 ሰንጋዎችን አበርክተዋል፡፡
በተወካዮቻቸው በኩል በምድር ኃይል ቅጥር ግቢ ድጋፉን ያስረከቡት አልጌ ሳቺ፣ ዳሪሙ እና ዶረኒ ወረዳዎች ነዋሪዎች ናቸው፡፡
የአገር መከላከያ ሠራዊቱ የሕግ ማስከበር ዘመቻ መጀመርን ተከትሎ ሕብረተሰቡ ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ድጋፉን እየሰጠ ይገኛል፡፡