ቀጥታ፡

የህውሃት ክህደት ከምስረታው ጀምሮ ይዞት የመጣው ባህሪው መሆኑን ምሁራን ገለጹ

ባህርዳር ህዳር 09/2013 (ኢዜአ) ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው የክህደት ወንጀል ከምስረታው ጀምሮ ይዞት የመጣው የአደገኛ ባህሪው ትክክለኛ መገለጫ መሆኑ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አስተያየታቸወን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን ገለጹ።

የጥፋት ቡድኑ በትጥቅ ትግሉም ሆነ በስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን አማራጭ ድምጾችንና ሃሳቦችን በማጥፋት ወደር የሌለው ድርጅት መሆኑን ምሁራን  አስታውሰዋል።

በዩኒቨርሲቲው የታሪክ ተመራማሪና መምህር ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ እንዳሉት  ህወሓት ከሃገርና ህዝብ ጥቅም በላይ ለድርጅት ህልውና የሚጨነቅ በመሆኑ ለውድቀት ተዳርጓል።

ከምስረታው ጀምሮ በትግራይ ውስጥ ከኔ በቀር ሌሎች ድርጅቶች መኖር የለባቸውም በማለት እንደ ኢዲዩ፣ ኢህአፓና ሌሎች ድርጅቶችን በማጥፋት ራሱን ብቸኛ የትግራይ ተወካይ አድርጎ የተጓዘ ቡድን  እንደሆነም ገልጸዋል።

ስልጣን ከያዘ ማግስት ጀምሮም እንደ ኦነግ እና ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችን ከማጥፋት ባሻገር ለሱ ሃሳብ ተገዥ ያልሆኑ ምሁራንና ግለሰቦች ጭምር ሲያስወገድ የኖረ ቡድን መሆኑን አመልክተዋል።

 ፕሮፌሰር ሹመት ይህን እኩይ ባህሪውን ከመሸገበት ትግራይ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ወንጀል በመፈጸም ሀገር ከሃዲነቱን ዳግም በተግባር አረጋግጧል ብለዋል።

ህወሓት  ከራሱ ፍላጎትና ጥቅም ውጭ ሌላ የማይታየው፣ ጥቅሜ ተነካ ብሎ ካመነ ሀገር ቢፈርስ ደንታ የሌለውና አደገኛ ጁንታ መሆኑንም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ በፈጸመው ጥቃት ማስመስከሩን አስረድተዋል።

ፕሮፌሰር ሹመት እንዳሉት ጁንታው ለሀገርና ህዝብ የሚጠቅም ነጻ ሃሳብ ያላቸውን የትግራይ ሽማግሌዎችና የህዝቡን አመኔታ ያገኙ ሰዎችን መንጥሮ በማጥፋት ደንታ ቢሰ ትውልድ ለመፍጠር ሞክሯል።

አማራጭ ድምጾች በማጥፋት በፀረ ዴሞክራሲያዊ መንገድና አምባገነን አገዛዝን በማስፈን እስካሁን  ድረስ በሀገሪቱ ለተከሰተው ግጭት፣ ሁከትና ብጥብጥ መንስኤ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ተግባር የትግራይ ህዝብ ቅድመ ታሪክ እንዳልሆነም የታሪክ ተመራማሪው አስታውቀዋል።

በህዝብ ትግል በመጣው ለውጥም የህወሓት አመራሮች የተሰጣቸውን ምህረት እንደ ጥቃትና አደጋ በመመልከት እልህ ውስጥ መግባታቸው ዛሬ ላይ ለተፈጠረው የመጨረሻው የእብሪተኝነት ችግር እንደዳረጋቸውም አስረድተዋል።

አሁን መንግስት እየወሰደ ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻም ጁንታውን በማስወገድ የትግራይን ህዝብ ነጻ ከማውጣት ባሻገር የሃገሪቱን አንድነት ለማስጠበቅ ያለውን ፋይዳ ሁሉም ሕዝብ ሊገነዘበው እንደሚገባ አብራርተዋል።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር እምቢአለ በየነ በበኩላቸው "ህወሓት በማይካድራ በንጹሃን ዜጎች ያካሄደው ጭፍጨፋ ግልጽ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው" ብለዋል።

ይህም በአምነሲቲ ኢንተርናሽናል ምርምሮች የተረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳትም የተዛባ ትርክት በመፍጠር በተባባሪዎቻቸውና በራሳቸው ጭምር ሕዝብ የመፍጀት ተግባር ሲፈጽሙ መቆየታቸውን አውስተዋል።

በመከላከያ ሠራዊቱ የተጀመረው የህግ ማስከበር ስራ ሲጠናቀቅ ከመረጃ የራቁና ለጊዜው የተደበቁ አስከፊ የንጹሃን ዜጎች ጭፍጨፋ ማስረጃዎች ሊወጡ እንደሚችሉም ገልጸዋል።

አሁን ላይ መንግስት የጀመረውን የህግ ማስከበር ስራ አጠናክሮ በማስቀጠል ዘመቻውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቀ ርብርብ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር በሰው ህይወት፣ ንብረትና ሃብት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት የከፋ  ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብም መንግስት እያደረገ ያለውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በመደገፍ የጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ምሁራኑ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም