በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው የልኡካን ቡድን ሩዋንዳን ጎበኘ - ኢዜአ አማርኛ
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው የልኡካን ቡድን ሩዋንዳን ጎበኘ
ህዳር 9/2013(ኢዜአ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በሩዋንዳ ጉብኝት አድርጓል።
ልኡካን ቡድኑ በአገሪቱ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት ለሩዋንዳው የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር ቪንሰንት ቢሩታ አስረድቷል።
ባለፉት ሁለት አመታት ተኩል በኢትዮጵያ ሲካሄድ የነበረው ለውጥ ባስገኛቸው ሁለገብ ጠቀሜታዎች ላይም ገለጻ አድርገዋል።
በተለይም የህወሃት ጁንታ ይህን ለውጥ ተጻርሮ መቆሙን፤ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አክራሪ ቡድኖችን ሲያደራጅ፣ በገንዘብ ሲደግፍና ሲያሰማራ መቆየቱን አብራርተዋል።
የአገሪቱን ህገ-መንግስት በመጻረር ህገ-ወጥ ምርጫ ማካሄዱንና ይህም በአገሪቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መወገዙን አስረድተዋል።
ይህ ቡድን የፌዴራል መንግስትን ህጋዊነት መጻረሩን፣ በቅርቡ ደግሞ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ከ20 ዓመታት በላይ በቆየው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ በውይይታቸው አንስተዋል።
የህወሃት ጁንታ በተለያዩ አካባቢዎች በሚኖሩ ሰላማዊ ህዝቦች ላይ ጥቃት ፈጽሞ የንጹሃንን ህይወት ማጥፋቱን፣ በዚህም ከብዙ ጊዜ ትዕግስት በኋላ የፌዴራል መንግስት የህግ ማስከበር ስራ መጀመሩን ልጸዋል።
የዚህ አላማም የህግ የበላይነትን በማስከበር አጥፊዎችን ለህግ ማቅረብና የአካባቢውን ህዝብ ነጻ ማውጣት መሆኑን አብራርተው፤ ወዳጅ የሆነው የሩዋንዳ ህዝብም ጉዳዩን በደንብ እንዲረዳው በማለት መልእክት አስተላልፈዋል።
የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር ቪንሰንት ቢሩታ በበኩላቸው ሩዋንዳ የኢትዮጵያ ወዳጅ አገር መሆኗን እና የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት አጥብቃ እንደምትመኝ ገልጸዋል።
ሩዋንዳ ሁልጊዜም ከኢትዮጵያ ጎን በጽናት እንደምትቆም፣ ስራው በአጭር ጊዜ የሰብአዊ መብትን ባከበረ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ጽኑ ፍላጎት እንዳላትም አረጋግጠዋል።
በውይይቱ ላይ የሩዋንዳው የደህንነት ሃላፊ ሜጀር ጄኔራል ጆሴፍ ዛባይታ በሚኒስትሩ የተሰጠውን አስተያየት አጠናክረዋል።
ውይይቱ በመግባባትና ወዳጅነትን በሚያጠናክር መልኩ መጠናቀቁን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው የልኡካን ቡድን ቀደም ብሎ በዩጋንዳ ከፕሬዝዳንት ዩወዬሪ ካጉታ ሙሰቬኒ እንዲሁም በኬንያ ከፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ጋር ተመሳሳይ ውይይት ማድረጉ ታወቃል።