ቀጥታ፡

በትግራይ የሚካሄደው ሕግ የማስከበር ሥራ ኢትዮጵያን በማተራመስ ላይ በተሠማሩ የሕወሐት ቡድን አባላት ላይ ያነጣጠረ ነው ... የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት

አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2013(ኢዜአ) በአሁኑ ወቅት በትግራይ የሚካሄደው ሕግ የማስከበር ሥራ በዋነኝነት ኢትዮጵያን በማተራመስ ላይ በተሠማሩ ሥርዓት አልበኞች፣ በተንኮልና በሤራ በተሞሉ የሕወሐት ቡድን አባላት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ማንም ሰው ጥርጣሬ ሊገባው አይገባም ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እና ሕገ ወጥ ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ ቁርጠኝነት ያለው መሆኑን በመግለጽ፤ ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ በብሔር ወይም በሌላ ወገንተኝነት ላይ የተቃኘ ነው የሚለውን የተሳሳተ እሳቤ አጥብቆ የሚያወግዝ መሆኑንም አስታውቋል፤፤

በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ ሳይቀር የከፋ በደል የሚፈጽመውን የሕወሐት ጁንታ የወንጀል ሰንሰለት ለማስቆም የፌዴራል መንግሥት ቆርጦ መነሳቱም ተጠቅሷል።

በሕግ ማስከበር ዘመቻ የትግራይ ሕዝብ የመጀመሪያው ተጠቃሚ እንደሚሆን በመግለጽ፤ ለኢትዮጵያ ያለው ራእይ በብዝኃነት የሚኮሩ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት የሚኖሩባት የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት መሆኑም ተጠቅሷል።

የትግራይ ሕዝብ ሕዝባችን ነው ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፤ ህወሃትን ከትግራይ ህዝብ መለየት እንደሚያስፈልግና በዚህ ሕዝብ ላይ ምንም ዓይነት ክፉ ነገር እንዲደርስ አንፈልግም፤ ይሄንን የሚያደርጉትንም አንታገሥም በማለት ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም