ለመከላከያ ሰራዊት የህግ ማስከበር ዘመቻ የአማራ ክልል ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል … አቶ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
ለመከላከያ ሰራዊት የህግ ማስከበር ዘመቻ የአማራ ክልል ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል … አቶ አገኘሁ ተሻገር
ባህርዳር፤ ህዳር 8/2013(ኢዜአ) የመከላከያ ሰራዊት የተያያዘውን ህግን የማስከበር እንቅስቃሴ የአማራ ክልል ህዝብና የፀጥታ ሀይል ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘው ተሻገር ገለጹ።
"ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ክብር እቆማለሁ "በሚል መሪ ሃሳብ የመከላከያ የክብር ስነ-ስርዓት በባህር ዳር ከተማ የክልሉ ርእሰ መስተዳደር በተገኙበት ተከብሯል።
ርዕሰ መስተዳደሩ በስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት የህወሓት ቡድን የመከላከያ ስራዊት ላይ ጥቃት በማድረስና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ትንኮሳ በማደረግ ግጭቱ እንዲፈጠር አድርጓል።
ቡድኑ የጀመረውን ጦርነት የአማራ ክልል ልዩ ሃይልና የሚሊሻ አባላት ከመከላከያ ስራዊት ጎን በመሆን ህግ ለማስከበር በሚደረገው ጦርነት ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
የሃገር የመከላከያ ሰራዊት የደረሰበትን የክህደት ጥቃት በመመከት እየተካሄደ ያለው የማጥቃት ዘመቻ ባጠረ ጊዜ በድል እንዲጠናቅቅ መላ ኢትዮጵያዊያን እያደረጉ ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።
"የመላ ኢትዮጵያዊያን የሞራልና የቁሳቁስ ድጋፍ ለመከላከያ ስራዊቱ ጉልበትና ብርታት ሆኖ መገኘቱን በቅርብ ስለምንገኝ መገንዘብ ችለናል" ብለዋል።
የክልሉ ህዝቦችና መላው ኢትዮጵያዊያን እያደረጉ ያሉት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እስከ ድሉ ማግስት ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቶ አገኘሁ አሳስበዋል።
"ለመከላከያ ክብር ሲባል በአገር አቀፍ ደረጃ የተደረገው የክብር ስነ-ስርአትና በእየለቱ በመላ ኢትዮጵያዊያን እየተደረገ ያለው የሞራልና የቁሳቁስ ድጋፍ የሰራዊቱን ጠላት ድል የመንሳት አቅም እያጎለበተው ነው” ያሉት ደግሞ የምዕራብ እዝ አባል ሃምሳ አለቃ የዓለም ዘውድ ጌትነት ናቸው።
በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመው የክህደት ወንጀል ታሪክ የማይረሳው መሆኑን ጠቅሰው፤ “አጥፊው ቡድን በጫረው እሳት እየተለበለበ ይገኛል” ብለዋል።
ባለፉት ቀናት በተደረገው ተጋድሎም ጠላት ድል መነሳቱን አመልክትው፤ በጀግናው ሰራዊት ያልተቆጠበ ውጊያም የድል ቀኑ ረጅም እንደማይሆን ተናግረዋል።
የአማራ ልዩ ሃይልና የሚሊሻ አባላት ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት እያደረጉት ያለው ተጋድሎ የሚመሰገንና ትልቅ ጉልበት መሆኑንም አመልክተዋል።
''ህወሓት ሲመሰረት ጀምሮ ህዝብ ጨፍጫፊና ገዳይ ቡድን ነው'' ያሉት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አድማ ብተና ሻለቃ አዛዥ ኮማንደር መኮንን ከሰተ ናቸው።
በተለይ የአማራን ህዝብ በጠላትነት ፈርጆ ሲገድልና ሲያሳድድ የቆየ ቢሆንም የኢትዮጵያዊያን ጋሻና መከታ የሆነው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ያልታሰበ የክህደት ጥቃት ማድረሱ የድርጅቱን ጫፍ የወጣ የኢትዮጵያ ጠላትነት ያስመሰከረ መሆኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ልዩ ሃይልና የሚሊሻ አባላትም ከመከላከያ ጎን በመሆን ቡድኑን ለመደምሰስ እየተደረገ ባለው ውጊያ እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸው “መንግስት በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረት ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።
በስነ-ስርአቱ ላይ የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች፣ የምዕራብ እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።