ቀጥታ፡

"ለሀገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ" የክብር ሥነ-ሥርዓት በኦሮሚያና ደቡብ ከተሞች ተከናወነ

ጊኒር/ፍቼ/ዲላ/ ህዳር 8/2013 በኦሮሚያ ምስራቅ ባሌና ሰሜን ሸዋ በደቡብ ክልል ደግሞ ጌዲኦ ዞኖች በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ክብርና ድጋፍ ገለጹ፡፡ 

በምስራቅ ባሌ ዞን የጊነር ከተማ ነዋሪዎች የክልሉንና  የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ  ይዘው አደባባይ በመውጣት  "ለመከላከያ ክብር እቆማለሁ” በሚል  በተዘጋጀው የክብር ሥነ-ሥርዓት  ላይ በመሳተፍ ድጋፋቸውን አሳይተዋል፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አብዳ አደም መንግስት በከሃዲው የህውሓት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት ለመከላከያ ሰራዊት ሲደርጉ የነበረውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት ደግሞ ሌለው የሥነ-ሥርዓቱ ተሳታፊ አቶ መሐመድ አሚኖ ናቸው፡፡

አቶ ጌታቸው ከበደ በበኩላቸው መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየወሰደ የሚገኘውን እርምጃ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

የምሥራቅ ባሌ ዞን የብልጽግና ፖርቲ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ እሸቱ በቀለ  የዞኑ ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊት ያለውን ድጋፍ በተለያዩ መንገዶች እየገለጸ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እስካሁን በጥሬ ገንዘብ  ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በተጨማሪም 164 ሠንጋዎችና ከ3ሺህ በላይ ፍያሎችን ለሠራዊቱ ድጋፍ መደረጉን አመለከተዋል።

ድጋፉን ያደረጉት አርሶና አርብቶ አደሮች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ባለሃብቶችና ሌሎች  የህብረተሰብ ክፍሎች  እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

የዞኑ  ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደም ቃሲም  የዞኑ ህብረተሰብ  ለመከላከያ ሠራዊትን በገንዘብና ዓይነት ከመደገፉም በሻገር አደባባይ በመውጣት ያለውን አጋርነት በማሳየቱ አመስግነዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት የፍቼ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተው ስሜታቸውን ዛሬ ገልጸዋል፡፡

የመንግስት ሰራተኞች ፣ የፖሊስ አባላትና ሌሎችም የህብረተሰብ  ክፍሎች በዚሁ በተዘጋጀው የክብር ሥነ-ሥርዓት  ለሠራዊቱ ያላቸውን ከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት  መፈፀማቸው የሚያኮራ መሆኑን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አጥናፉ በቀለ ገልፀዋል፡፡ 

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ብርሃኑ  የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተባብረውና ተከባብረው የውስጥና የውጭ ጠላት የማንበርከክ የቆየ ታሪካቸውን በከሃዲው ህውሐት ቡድን ላይ በድል አድራጊነት እንደሚደግሙ ገልጸዋል፡፡ 

ዝግጅቱ ሠራዊትን የሚበረታታ ከመሆኑም  ባሻገር በተቋማትና ሕዝቦች መካከል ጠንካራ ግንኙነት እንዲፈጠር እድል የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 


በሥነሥርዓት ከተካፈሉት መካከል  የፍቼ ከተማ አስተዳደር መምህራን ማህበር ተወካይ አቶ ገረሱ ደበሌ ሠራዊቱ በሀገሪቱ እያከናወነ ያለው ህግና ስርዓት የማስከበር እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ 


በቅርቡም የአንድ ወር ደመወዛቸውን ከመስጠት ባሻገር ደም በመለገስ አጋርነታቸውም ማሳየታቸውን  ጠቅሰዋል፡፡ 


የዞኑ ን ፖሊስ መምሪያ አባል ኮማንደር አበበ ደላሳም አጥንትና ደሙን ለሀገር ጥቅም ከሚያውል ሠራዊት ጐን በመቆም የሚፈለግባቸውን ለማበርከት እንደተዘጋጁም ገልፀዋል፡፡ 

በተመሳሳይ  በጌዴኦ ዞን የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ክብርና ድጋፍ ገልጸዋል።

በዲላ ከተማ በነበረው ሥነ-ሥርዓት ከተሳተፉት መካከል አቶ ዳንኤል ካብትይመር በከሃዲው የህወሓት ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

የሀገር  መከታ   በሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ የተቃጣውን ጥቃት በጽኑ እንደሚያወግዙ የገለጹት ደግሞ አቶ ሾጣ ገብሩ ናቸው።

የመከላከያ ሠራዊትን የደፈረው ጁንታው የህወሓት ቡድንን ለህግ ለማቅረብ የሚደረገውን ዘመቻ እንደሚደግፉም አስታወቀዋል።

በጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፖርቲ ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ተቋማትና ምሁራን አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ይመኑ ዳካ በበኩላቸው  ለመከላከያ ሠራዊተ ድጋፍ የሚውል ከ22 ሚሊዮን  ብር በላይ ከዞኑ ህብረተሰብ  የማሰባሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።


ሳጅን ከተማ ገለታ በሰጡት አሰተያየት በሠራዊቱ ላይ የተፈጸው የጭካኔ ተግባር ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንደሆነና በማንኛውም መንገድ ከሠራዊቱ ጎን ለመሰለፍ ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። 


የዲላ የኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ ለሀገርና ለወገን ጸር በሆኑት ሕገ-ወጥ ቡድኖች ላይ መንግሥት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም