የአገር መከላከያ ሠራዊት በህወሓት ቡድን ሲካድ የመጀመሪያው አይደልም---የጦር አካል ጉዳተኞች - ኢዜአ አማርኛ
የአገር መከላከያ ሠራዊት በህወሓት ቡድን ሲካድ የመጀመሪያው አይደልም---የጦር አካል ጉዳተኞች
አዲስ አበባ ህዳር 8/2013 (ኢዜአ) "የህወሓት ከሃዲ ቡድን የአገር አንድነትና ሉዓላዊነት ዘብ የሆነን መከላከያ ሠራዊት መክዳት ከጥንስሱ ያዳበረው የክህደት ባህሪው ነው" ሲሉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አካል ጉዳተኞች ተናገሩ።
መንግስት በጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ላይ በጀመረው ሕግ የማስከበር ተልዕኮም ቀሪ አካልና ንብረታቸውን በመስጠት ለመስዋዕትነት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
'ለአገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ' በሚል ዛሬ በተካሄደው አገር አቀፍ ትዕይንት በተሽከርካሪ ወንበር መጥተው ለሠራዊቱ ያላቸውን ክብር ለመስጠት ትዕይንቱን የታደሙ ኢትዮጵያዊያንም ነበሩ።
እነዚህ አካል ጉዳተኞች በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ በመሰሪ ድርጊቱ ጭፍጨፋ ያደረሰው ከሃዲው ህወሓት ገና ኢትዮጵያን ከመቆጣጠሩ በፊት ለአገራቸው ዘብ በመቆም ክቡር ገላቸውን የቆረሱ የቀድሞው ጦር ሠራዊት አባላት ናቸው።
ጦር ሠራዊቱን ለዘጠኝ ዓመታት ያገለገሉት መቶ አለቃ ጥላዬ ሽፈራው ከ1977 ዓ.ም ለአገራቸው አንድነት ሲዋደቁ አካላቸው የጎደለ መሆኑን ገልጸው፤ ህወሓት አገሪቷን በበላይነት ሲቆጣጠር 'የደርግ ሠራዊት በሚል ተለጣፊ ስም በትኖናል' ይላሉ።
"ጽንፈኛው ህወሓት ከኮንጎ እስከ ኮሪያ፣ ከሶማሊያ እስከ ላይቤሪያ ጀብዱ የፈጸመ፣ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ዝና ያካበተ፣ አኩሪ ገድል ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ያዋረደ ከሃዲ ቡድን ነው" ይሉታል።
የጥፋት ቡድኑ ገና ከጅምሩ ከ30 ዓመታት በላይ የተገነባ የአገር አጥር የሆነን ሠራዊት በመበተን ክህደት መፈጸሙን አውስተው፤ አሁንም በሠራዊቱ ሪፎርም መሰራቱን ተከትሎ በድጋሚ ክህደት መፈጸሙን ይናገራሉ።
በ1980ዎቹ የቀድሞውን ጦር ሠራዊት ተቀላቅለው ለሦስት ጊዜ ከቆሰሉ በኋላ በአራተኛው ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን የተናገሩት አስር አለቃ ጸጋዬ መገርሳ በበኩላቸው፣ "እኛ የተዋጋነው አገር እንዳትበተንና ለህዝብ ደህንነት ነበር" ይላሉ።
ህወሓት አገሪቷን ከተቆጣጠረ በኋል ግን "የጦር አካል ጉዳተኛ የሚለውን ስም ሳይቀር በመቀማት አካል ጉዳተኛ እንድንባል በማድረግ አገራዊ ለውጡ እስከሚጣ ድረስ የከፋ ተጽዕኖ ሲያደርስብን ቆይቷል" ብለዋል።
ከዚህም አልፎ አካል ጉዳተኞቹ ከነበሩበት "የጀግኖች አምባ" ከተባለ ስፍራ እንዳስወጣቸው፣ በኋላም "በአዲስ አበባ ወንዝ ተጥለን ከ60 በላይ አባላት በሁለት ወር ውስጥ ለሕልፈት ተዳርገዋል ሲሉ ይናገራሉ።
የቀድሞ ጦሩንም የበተነ፣ አገሩን የዘረፈ ቡድን ዛሬም አልጋውን አፈር፣ ትራሱን ድንጋይ፣ ልብሱን ብርድና ጸሐይ አድርጎ ለአገር ሉዓላዊነት ዘብ የቆመን ሠራዊት አዘናግቶ በመግደል ክህደት በመፈጸሙ አወግዘውታል።
ይህን ድርጊት ወራሪ ጠላት እንኳን ያልፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት እንደሆነ ገልጸው፤ የአገሩን አጥር ያፈረሰና ሠራዊቱን የከዳው ቡድን ለሕግ መቅረብ እንዳለበት ይገልጻሉ።
ሌላው የቀድሞ ጦር አካል ጉዳተኞ አቶ አለማየሁ ዓለሙ "የህወሓት ጁንታ ገና ከጅምሩ ጀምሮ የፈጸመው ድርጊት ከወታደራዊ ዲሲፕሊን ያፈነገጠ፣ ሰዎቹም ቆዳቸው እንጂ በውስጣቸው ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ናቸው" ይላሉ።
ጽንፈኛው ቡድን አገራዊ አንድነትን የሚወዱ የተለየ ሀሳብ ያላቸውን የራሱን አባላት ሳይቀር እየገደለ መምጣቱን በማስታወስ፣ ስልጣን ላይ ሆኖም መንግስታዊ ሽብር ሲያደርግ የቆየ መሆኑን ገልጸዋል።
የጦር አካል ጉዳተኞቹ እንደሚሉት ከጥንስሱ ጀምሮ ከህደት ለፈጸመው የህወሓት ቡድን "ድርድር ሳይሆን ሰንኮፉ ነው መነቀል ያለበት" ባይ ናቸው።
በዚህም መንግስት ከሃዲውን ቡድን ለሕግ ለማቅረብ በሚያደርገው ጥረት በቀሪ አካላቸውና ንብረታቸው እስከ ሕይወት መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።