ቀጥታ፡

የመከላከያ ሠራዊት በትግራይ በምሥራቅና በምዕራብ ግንባሮች ወሳኝ ድሎችን ተቀዳጅቷል

ህዳር 8/2013( ኢዜአ) የመከላከያ ሠራዊት ዛሬ በትግራይ በምሥራቅና በምዕራብ ግንባሮች ወሳኝ ድሎችን መቀዳጀቱ ተገለጸ።

በምሥራቁ ግንባር ራያን ሙሉ በሙሉ ነጻ ያወጣ ሲሆን፤ ጨርጨር፣ ጉጉፍቶ መሖኒንም ሠራዊቱ ነጻ አውጥቷል።

በየቦታው የነበሩ ወሳኝ የኮንክሪት ምሽጐችንም በማፍረስ ሠራዊቱ በአሁኑ ጊዜ ወደ መቀሌ በመገሥገሥ ላይ መሆኑም ተጠቅሷል።

በምዕራብ ግንባር ደግሞ በአዲ ነብሪድና በአዲ ዳእሮ የሚገኙ ከባድ ምሽጎችን በማፍረስ ሽሬን ተቆጣጥሮ ወደ አኩስም በመገሥገሥ ላይ እንደሆነም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ አስታውቋል።

በውጊያው እጅግ ብዙ መሣሪያዎች ከመማረካቸውም በላይ ህወሓት ለክፉ ዓላማው ያሰለፋቸው የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ የህወሓት ጁንታን በሕግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል እየገሠገሠ ሲሆን የጁንታው ኃይል የመከላከያ ሠራዊቱን ክንድ መቋቋም አቅቶት ወደኋላ እየሸሸ መሆኑን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም