ቀጥታ፡

ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም በሙያችን ሃላፊነታችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን - የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 8/2013 (ኢዜአ) ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም በሙያችን የሚጠበቅብንን ሃላፊነት እንወጣለን ሲሉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች ገለፁ።

የተቋሙ ሠራተኞች "ለአገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ" በማለት ለሠራዊቱ ያላቸውን ክብርና አጋርነት ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብና በጭብጨባ ገልፀዋል።

መርሃ ግብሩ ሲጠናቀቅ አስተያየታቸውን የሰጡ ሠራተኞችና አመራሮች በማንኛውም ሁኔታ ለመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፋቸውን ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

አገርና ሕዝብ ከጠላት ለመጠበቅና ለመከላከል ሕይወቱን በሰጠው ሠራዊት ላይ በአጥፊው የህወሓት ቡድን የተፈፀመውን ጥቃትም 'አሳፋሪ' ሲሉ አውግዘዋል።

የሕዝብ ደህንነት በማስጠበቅ ላይ እያለ በወገኑ ጥቃት የተፈፀመበት ይህ ሠራዊት ታሪክ የማይረሳውና ሲታወስ የሚኖር እንደሆነም ተናግረዋል።

የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ "የኢትዮጵያ ሠራዊት ማለት የአገር ሕዝብ ማለት ነው፤ ሠራዊቱ የሕዝቡ የሉዓላዊነት መገለጫ ነው፤ ጥቃቱ የደረሰው በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ነው" ብለዋል።

'በአገርና በሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ችግር ለመከላከል ከሠራዊቱ ጎን በመሆን እየሰራን ነው' ያሉት አቶ ሰይፈ የተቋሙ አመራርና ሠራተኛ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

ሠራዊቱ ከአገር አልፎ ለጎረቤት አገራት ደህንነት ዘብ የቆመ የአፍሪካ ኩራት መሆኑን የጠቀሱት ሠራተኞቹ  በጁንታው ኃይል የተፈፀመውን ክህደት አውግዘዋል።

መላው ሕዝብ እያሳየ ያለውን አብሮነትና አገር ወዳድነት አጠናክሮ በመቀጠል ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰሜን ዕዝ ጦር ላይ ጥቃት ከተፈፀመ ጀምሮ ሁኔታውን በመከታተል በዜናና በተለያዩ ፕሮግራሞች ለሕዝቡ ትክክለኛ መረጃዎችን እያደረሰ ይገኛል።

ጋዜጠኞችና የካሜራ ባለሙያዎቹን የሕግ ማስከበር ስራው በሚከናወንበት ስፍራ በማሰማራት ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን በማድረስም አጋርነቱን እያሳየ ነው።

በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የተዘጋጀው "ለአገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ" መርሃ ግብር መከላከያ ሠራዊት እየወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበርና የአገር ሕልውና የማስጠበቅ እርምጃ ለመደገፍ ያለመ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም