የሀዲያ ዞን ነዋሪዎች ለአገር መከላከያ ሰራዊት 53 ሰንጋ በሬዎችን ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የሀዲያ ዞን ነዋሪዎች ለአገር መከላከያ ሰራዊት 53 ሰንጋ በሬዎችን ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 8/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የሀዲያ ዞን ነዋሪዎች በትግራይ ክልል ህግ ማስከበር ዘመቻ ላይ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት 53 ሰንጋ በሬዎችንና 31 በግና ፍየሎችን ድጋፍ አደረጉ፡፡
ለመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ዞኑን ወክለው ድጋፉን ያስረከቡት የሥራ ኃላፊዎች ተናግረዋል።
ከዞኑ የተወከሉ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ነዋሪው ያበረከተውን ድጋፍ በመከላከያ ሚኒስቴር ምድር ኃይል ግቢ ተገኝተው አስረክበዋል፡፡
የሀዲያ ዞን ሰላምና ጸጥታ መመሪያ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ካቢሶ፣ የዞኑ ነዋሪዎች የህወሓት ዘራፊ ቡድን በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰውን እኩይ ተግባር በሰላማዊ ሰልፍ ማውገዛቸውን ገልጸዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም ነዋሪዎቹ ለሠራዊቱ ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት 53 ሰንጋ በሬዎችንና 31 በግና ፍየሎችን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የሀዲያ ዞን ነዋሪዎች ለአገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ አለማየሁ አረጋግጠዋል።
የዞኑ ነዋሪዎች በቀጣይም ለመከላከያ ሠራዊቱ 281 ሰንጋ በሬዎችን እንዲሁም 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸው ታውቋል።
ሌላው የዞኑ ተወካይ ኮማንደር አዲሱ ፈይሣ "የትግራይን ህዝብ የማይወክሉ ጥቂት የጥፋት ቡድኖች በፈፀሙት ተግባር ሁላችንም አዝነናል" ብለዋል።
አጥፊውን ቡድን ለማስወገድ በአገር መከላከያ ኃይል እየተወሰደ ያለው የህግ ማስከበር ዘመቻ እስኪጠናቀቅ ድረስ የዞኑ ነዋሪዎች ድጋፍ እንደማይለይም አረጋግጠዋል።
ከሀዲያ ዞን ነዋሪዎች የተደረገውን ድጋፍ የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለአገር መከላከያ ሠራዊት እያደረገ ያለው ድጋፍ ሁሉንም አኩርቷል ብለዋል።
በሀዲያ ዞን ነዋሪዎች በዛሬው ዕለት ለተደረገው ድጋፍም በዞኑ ተወካዮች በኩል የምስጋና መልእክታቸውን አድርሰዋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ህግ የማስከበር ዘመቻውን ከጀመረበት እስካሁን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ነዋሪዎች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡