የህወሀት ቡድን እያቀረበ ያለው የድርድር ጥያቄ ተቀባይነት የለውም -የጋሞ አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
የህወሀት ቡድን እያቀረበ ያለው የድርድር ጥያቄ ተቀባይነት የለውም -የጋሞ አባቶች
አርባምንጭ፣ ህዳር 8/2013 (ኢዜአ) የህወሃት ጁንታው ቡድን እያቀረበ ያለው የድርድር ጥያቄ ጊዜ ያለፈበትና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የጋሞ አባቶች ገለጹ፡፡
ቡድኑ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃት በብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ላይ የተፈጸመ መሆኑን የጋሞ አባቶቹ ለኢዜአ አስታውቀዋል ።
ከጋሞ አባቶች መካከል አቶ ሰዲቃ ስሜ በሰጡት አሰተያየት የህወሃት ጽንፈኛው ቡድን ለህዝቡ በቆመ መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት የአሸባሪነት ተግባር ነው፡፡
"ድርጊቱ የሀገር ክህደትና የህዝብ ንቀት ማሳያ ነው" ብለዋል።
ጥቃቱ ከ80 በላይ በሆኑ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ላይ የተፈጸመ አረመንያዊ ድርጊት እንደሆነም ተናግረዋል ።
ቡድኑ ለህገ-መንግስት ባለመታዘዝ ህገ-ወጥ ምርጫ ከማካሄድም በላይ አሸባሪዎችን በማሰልጠን በዜጎች ላይ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት በማድረስ የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ነው " ብለዋል ።
መንግስትና ህዝብ የቡድኑን እኩይ ተግባር ከሚገባው በላይ በመታገስ በኃይማኖት አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎችና በታዋቂ ሰዎች ሰላም ለማስፈን ሲማጸኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል ።
የጥፋት ቡደኑ በፈጸመው ድርጊት ሳይጸጸት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመደራደር እያቀረበ ያለው ጥያቄ ጊዜ ያለፈበትና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስታውቀዋል።
የወንጀለኛው ቡድን የአደራድሩኝ ጥያቄ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል።
"ከህወሃት ጽንፈኛ ቡድን ጋር መደራደር የኢትዮጵያን ህዝብ ህልውና እንደመሸጥ የሚታሰብ ነው" ያሉት አቶ ሰዲቃ መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ።
ሌላው የጋሞ ሀገር ሽማግሌ ካዎ ሙሉጌታ መንሳ የጥፋት ቡድኑ እያቀረበ ያለው የድርደር ጥያቄ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል ።
"መንግሰት የጀመረውን ህግ የማስከበር ስራ በድርድር ሰበብ ካቆመ ቡድኑ በህዝብ ላይ በደል ከመፈጸም ወደ ኋላ አይልም" ብለዋል።
"ከውጭ ወራሪ በላይ የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው የህወሀት ቡድን በድርድር ይቅር አይባልም" ሲሉ ካዎ ሙልጌታ አስታውቀዋል።
"ትግራይን ጨምሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነቱን የሚያገኝበት ጊዜ አሁን ነው" ያሉት ደግሞ ካዎ መንግስቱ ደምሴ ናቸው።
መንግስት በኢትዮጵያ ህዝብ ባህል መሠረት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥረትና ሰፊ ትዕግስት ሲያደርግ መቆየቱን አሰታውሰዋል ።
"ቡድኑ አሻፈረኝ በማለት ዘግናኝ ድርጊት እየፈጸመ ህዝብን የበለጠ ማሳዘኑን ቀጥሎበታል" ያሉት ካዎ መንግስቱ ቡድኑን ከህግ ሌላ ሊዳኘው የሚችል አማራጭ እንደሌለ አስታውቀዋል።
መንግስት የጀመረው ህግ የማስከበር ስራ ተጠናከሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስታውቀዋል ።