ቀጥታ፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ደም ለገሱ

አሶሳ፣ ሕዳር 08 / 2013( ኢዜአ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ደም በመለገስ ለሃገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ድጋፍና አጋርነት ገለጹ። 

አመራሮቹ በደም ልገሰ መርሃ ግብሩ ወቅት  እንዳሉት ህወሓት በሃገር መከላከያ ላይ የፈጸመው ጥቃት ለማመን የሚከብድ እጅግ አስነዋሪ ድርጊት ነው፡፡

ደም ከለገሱት መካከል የብልጽግና ፓርቲ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢስሃቅ አብዱልድር በሰጡት አስተያየት  መከላከያ ሠራዊት ከሃገር አልፎ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት መከታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ህወሓት ከትግራይ ቀጥሎ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ሁለተኛ ክልሉ በማድረግ በሞግዚት ሲያስተዳድር እንደነበር  አስታውሰዋል፡፡

ይህንን የሚያስፈጽሙ አባላቱን በክልሉ በየከተሞች እና ጠረፍ አካባቢ ማስቀመጡን ጠቅሰው ከክልሉ ተወላጆች ጭምር አባል አፍርቷል ብለዋል፡፡

ከለውጡ በኋላም ክልሉ እንዳይረጋጋ እና የጦር አውድማ እንዲሆን ሲሰራ መቆየቱን አቶ ኢስሃቅ ተናግረዋል፡፡

በአጥፊው ቡድን ላይ ህግን የማስከበር እርምጃ መውሰድ ከተጀመረ በኋላ በርካታ የቡድኑ ተላላኪዎች ለተጨማሪ ጥፋት በክልሉ ህገ-ወጥ ገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ይዘው ሲንቀሳቀሱ  በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስረድተዋል፡፡

የህወሓት ተላላኪዎችን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የሚደረግ ጥረት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ኢስሃቅ አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ ሴቶች ህጻናት እና ወጣቶች ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሂጂራ ኢብራሂም በበኩላቸው የእናት ጡት ነካሽነቱና  የከሃዲነቱን ድርጊት ህወሓት በሚገባ በተግባር አሳይቷል ብለዋል፡፡

መከላከያ ለሃገሩ ስለከፈለው መስዋዕትነት ለመግለጽ ቃላት እንደሚያጥራቸው የሚናገሩት ከፍተኛ አመራሯ ለሠራዊቱ ደም ብቻ ሳይሆን ህይወትም ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በከሃዲው የህወሓት ቡድን አባላት ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ተገቢ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት  አፈ-ጉባኤ አቶ ታደለ ተረፈ ናቸው።

ይህም በቀጣይ  ህዝብን ለመካስ የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ ያግዛል ያሉት ከፍተኛ አመራሩ የክልሉ ምክር ቤት ድጋፉን እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ ስፖርት  ኮሚሽነር አቶ አስር ኢብራሂም  የህወሃት ጥፋት ቡድን እንደራደር ጥያቄ መቀበል የኢትዮጵያ ህዝብን እንደመካድ ይቆጠራል ብለዋል።

ህግን የማስከበር እርምጃው የትግራይ ህዝብን ነጻ የሚያወጣና የናፈቀውንም ሠላም የሚመልስ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም