ቀጥታ፡

ስግብግቡ የህወሓት ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት ታሪክ ይቅር የማይለው ነው...አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ፤ ህዳር 8/2013(ኢዜአ) ስግብግቡ የህወሓት ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት ታሪክ ይቅር የማይለው ነው ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ። 

የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ጽንፈኛው የህወሓት ቡድንን ድርጊት በመቃወም ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን አጋርነትና ድጋፍ ትላንት በሠላማዊ ሠልፍ ገለጹ። 

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በጋምቤላ ከተማ በተካሄደው ሰልፍ ላይ ባደረጉት ንግግር ስግብግቡ የህወሓት ቡድን ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ህዝቦች እርስ በእርስ በማጋጨት የዜጎች ህይወት እንዲጠፋ ከማድረግ ባለፈ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና የዘረፋ ወንጀሎችን ሲፈጽም መቆየቱን አስታውሰዋል።

ህወሓት በነበረው እኩይ ድርጊቱ በህዝብ ተቃውሞ ተገፈቶ ከወጣ በኋላም ከኦነግ ሸኔ ጋር የጥፋት ጋብቻ በመፈጸም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ የበርካታ የዜጎች ህይወትና ንብረት እንዲጠፋ ማድረጉን አስረድተዋል።

ጽንፈኛው ቡደን የኢትዮጵያ እድገት ከማይፈልጉ የውጪ ኃይሎች ጋር በማበር የሀገርና የህዝብን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት ጭምር ሲሰራ ነበርም ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት የጥፋት ቡድኑ ለሁለት አስርት ዓመታት የትግራይን ህዝብ ሠላምና የሀገርን ድንበር ሲጠብቅ በነበረው የመከለከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱ አረመኔያዊ ክህደት ፈጽሟል።

የከሃዲ ቡድን ሴራን ለማምከን በመንግስት የተጀመረው ህግን የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቀሙው፤ ለተግባራዊነቱም ህዝቡ ከሠራዊቱ ጎን እንዲሰልፍም አሳስበዋል።

የጋምቤላ ክልል በጥፋት ቡድኑ ለግጭት ከታለሙት አካባቢዎች አንዱ እንደሆነ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ ህዝብ የጥፋት ኃይሉን ሴራ ለመመከት የአካባቢውን ሠላም ነቅቶ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።

ሰልፈኞቹ የሀገር መከላከከያ ሠራዊትን የሚያበረታቱና  ከሀዲውን የህወሓት ቡድንን  የሚያወግዙ የተለያዩ መፈክሮችን አሰምተዋል።

በህወሓት ተላላኪዎች በየቦታው የሚፈጸመው ብሔር ተኮር ግድያዎችን እንቃወማለን፣ ህግን ለማስከበር በጥፋት ቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት እና  የሉአላዊነታችን ጋሻና መከታ የሆነውን ጀግና መከላከያ ሠራዊታችንን በሙሉ አቅማችን ከጎኑ እንቆማለን የሚሉት ሠልፈኞቹ ካሰሟቸው መፈክሮች ናቸው።

የሠልፉ ተሳታፊ አቶ ኡቦንግ ጋሜ በሰጡት አስተያየት የህወሓት ጽንፈኛ ቡድን  በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን እኩይ ተግባር ለማውገዝ መውጣታቸውን ተናግረዋል።

መንግስት በከሃዲው ህወሓት ላይ እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃን  በመደገፍ ጭምር ሠልፉን መቀላቀላቸውን ጠቁመው፤ ከሠራዊት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የህወሓት የጥፋት ቡድን የሀገርን ዳር ድንበር እየጠበቀ በነበረው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት ለማውገዝና  ለመቃወም የሠልፉ ተሳታፊ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የኢዜማ አባል አቶ ኡፑቲ አኳይ ናቸው።

አሸባሪ ቡድኑ ላይ መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው፤ ከመንግስት ጎን በመሆን የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ወይዘሮ መሰረት መልኪያስ  በበኩላቸው  የህወሓት ቡድን በሠራዊቱ ላይ የፈጸመው የክህደት ተግባር አሳፋሪ መሆኑን በመግለጽ ድርጊቱን ኮንነዋል።

በሠላማዊ ሠልፉ የሀገር ሽማገሌዎች፣ ወጣቶች ፣የመንግስት ሰራተኞች፣ ተማሪዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም