በመቐለ የአየር ጥቃት መደረጉን በተመለከተ የወጡት ቪዲዮዎች ሐሰተኛ ናቸው- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
በመቐለ የአየር ጥቃት መደረጉን በተመለከተ የወጡት ቪዲዮዎች ሐሰተኛ ናቸው- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ኃይል
አዲስ አበባ፣ ህዳር 8/2013 (ኢዜአ) በሁለት ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን አማካኝነት በመቐለ የአየር ጥቃት መደረጉን የሚገልጹ አርዕስት እና አጭር ቪዲዮዎች ሐሰተኛ መሆናቸውን የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ ኃይል መረጃ ማጣሪያ አስታወቀ፡፡
በሁለት ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን አማካኝነት፣ በመቐለ የአየር ጥቃት መደረጉን የሚገልጹ አርዕስት እና አጭር ቪዲዮዎች ወጥቷል።
እነዚህ መረጃዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ኃይሉ ሳይረጋግጡ በሕወሐት መረጃ ላይ ብቻ የተመሠረቱ ሐሰተኞች መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በሂደቱ ውስጥ ሰላማዊ ሰዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል የሚለው መረጃም እንዲሁ ሐሰት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመሥርቶ በወሳኝ የሕወሕት ዒላማዎች ላይ ከመቀሌ ከተማ ውጭ የታለመ የአየር ጥቃት አካሂዷል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕግ የበላይነትን የማስከበር እንቅስቃሴ ዒላማን በጥንቃቄ መምታትን መሠረት ያደረገ ነው።
ሕወሐት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃቱን ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ፣ የመከላከያ ሠራዊቱ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት ሲል ከከተሞች የራቀ ጥቃት ላይ ማተኮሩን የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ ኃይል መረጃ ማጣሪያ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።