በደቡብ ክልል ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚውል ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚውል ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ
ሀዋሳ፣ ህዳር 07/2013(ኢዜአ) በደቡብ ክልል ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ የሚውል ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና ዓይነት መሰብሰቡን የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ አስታወቀ ፡፡
የቢሮው አቶ ተፈሪ አባተ በድጋፍ አሰባሰቡ ዙሪያ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን መከላከያ ሠራዊትን ባልጠበቀበት ሁኔታ ከጀርባው በመውጋት አሳፋሪ የሀገር ክህደት ተግባር ፈጽሟል፡፡
መንግስት ይህ የጥፋት ቡድን በህግ እንዲጠየቅ ለማድረግ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አመልክተው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ቀፎው እንደተነካበት ንብ በመነቃነቅ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን መቆሙን እየገለፀ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ደቡብ ክልል የህዝብ ድጋፍ በተገቢው መንገድ ለመምራት በቢሮው ሰብሳቢነት የሚመራ ዐብይ ኮሚቴ መዋቀሩን ተናግረዋል።
ከተያዘው ወር መግቢያ ጀምሮ በክልሉ የሚገኙ አመራሮች፣ የተለያዩ ተቋማት፣ ሠራተኞችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርጉት ድጋፍ ወጥ በሆነ መንገድ እየተሰበሰበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
"በክልል ደረጃ ያሉ ተሿሚዎች የአንድ ወር ደመወዛቸውን እንዲሁም ከክልል ማዕከል ሰራተኞችና ተቋማት ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል" ብለዋል፡፡
በስድስት ዞኖች ግምቱ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብና ዓይነት ድጋፍ መገኘቱን ጠቁመዋል።
እስካሁን በአጠቃላይ ከ52 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡንና ከዚህ ውስጥ 16 ሚሊዮን 400 ሺህ ብር ግምት ያለው በዓይነት የተሰበሰበ መሆኑን አስታውቀዋል።
በክልሉ ድጋፍ የማሰባሰብ ንቅናቄ እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዷል።