ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ የ20 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ የ20 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
ፕሮጀክቱ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ለስድስት ወራት የሚተገበርና 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡
አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶችና ህጻናትና በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ሥራ በማጣት ለችግር የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ መስፍን ተክለአብ ፕሮጀክቱ መንግስት ኮሮናቫይረስን ለመከላከልና በወረርሽኙ ምክንያት የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
17 የሲቪክ ማኅበራት ለፕሮጀክቱ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አቶ መስፍን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት መድረክ ቀደም ሲልም ከአባላቱ ደመወዝ ባሰባሰበው ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የኮሮናቫይረስ መከላከያና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው ድጋፉ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ሕብረተሰቡ በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚደረገውን ድጋፍ በአግባቡ በመጠቀም ራሱን ከቫይረሱ እንዲጠብቅም አስገንዝበዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ስለ ቫይረሱ ግንዛቤ የሌላቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች በመለየት በራዲዮና በሌሎች የመረጃ ማሰራጫዎች ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ከክልሎች ጋር በመነጋገር በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለጉዳት የተጋለጡ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ሥራም ይከናወናል።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ጂማ ዲልቦ የሲቪክ ማኅበራት ወረርሽኙን ለመከላከል ከመንግስት ጎን ሆነው የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።
ኅብረተሰቡ ኮሮናቫይረስ ጠፍቷል በሚል እየተዘናጋ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ በመሆኑ በጤና ሚኒስቴር የተቀመጡ መመሪያዎችን ያለመዘናጋት መተግበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ኮሮናቫይረስ ከኢትዮጵያ እስኪጠፋ ለኅብረተሰቡ ትምህርት በመስጠትና ድጋፍ በማድረግ ትብብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።