ለአፍሪካም ለኢትዮጵያም በኦሊምፒክ በሴቶች የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳሊያ የተገኘበት እየተዘከረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለአፍሪካም ለኢትዮጵያም በኦሊምፒክ በሴቶች የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳሊያ የተገኘበት እየተዘከረ ነው
አዲስ አበባ ህዳር 7/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአፍሪካም በኢትዮጵያ በኦሊምፒክ በሴቶች የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ የተገኘበትን የባርሴሎና ኦሊምፒክ ቀንን ዛሬ እየዘከረ ነው ።
ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1956 ሜልቦርን ጀምሮ በ13 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለእያንዳንዱ ቀን በመመደብ በዚህ ወር እየዘከረች ነው።
በዚህ መሰረትም ዛሬ ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ለሰባተኛ ጊዜ በተካፈለችበት የባርሴሎና ኦሊምፒክ የተካፈሉ አትሌቶችን ተሳትፎና ውጤት እየታሰበ ነው።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1984 በተካሄደው ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ በዘጠኝ ወንዶችና በስድስት ሴቶች ተወክላ ነበር።
በዚህ ኦሊምፒክ ከተካፈሉት ውስጥ አሁን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ደራርቱ ቱሉ ድል ይታወሳል።
በዚህ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ አበበ ቢቂላ በማራቶን ሮም ላይ የተመዘገበው ዓይነት ድል በሴቶች ደግሞ እንደ አገርም ሆነ እንደ አፍሪካ የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳሊያ በ10 ሺህ ሜትር ሩጫ የተገኘበት ነው።
ደራርቱ ቱሉ የአፍሪካ ሴቶች ፈር ቀደጅ በመሆን በዚህ ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ ታሪክ ሰርታለች።
አትሌት ደራርቱ ያን ጊዜ ስታሰታውስ ''በወቅቱ እሷን የጠበቀ እንዳልነበርና የሁሉም ዓይን በደቡብ አፍሪካዊቷ አትሌት ኤሊና ሜየር ላይ ነበር" ትላለች።
ከኦሊምፒክ መልስ ከ10 አለቃነት ማዕረግ ወደ ሻለቃነት ደረጃ ያደገችበትና ደሞዟም ከ200 ብር ወደ 600 ብር እንዳደገ የታሪክ ማህደሯ ያሳያል።
አትሌት ፊጣ ባይሳ በ5 ሺህ ሜትር፣አዲስ አበበ ደግሞ 10 ሺህ ሜትር ሩጫ የነሐስ ሜዳሊያዎች ያስገኙበት ኦሊምፒክም ነበር።
ኢትዮጵያ በአንድ ወርቅና በሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎች በኦሎምፒኩ ከተሳተፉ አገሮች በአትሌቲክስ ዘርፍ ከአፍሪካ ሶስተኛ ከዓለም ደግሞ 12ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች፡፡
ፌደሬሸኑ ነገ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የ1996 አትላንታ ኦሊምፒክ አትሌቶች ያስመዘገቡትን ድል ይዘክራል።