ቀጥታ፡

የህወሃት ቡድን የትግራይ ወጣቶችን እኔ ከሌለሁ መኖር አትችሉም እያለ ሲያደናግር ኖሯል- በቁጥጥር ስር የዋሉ የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት

አዲስ አበባ ህዳር 7/2013 (ኢዜአ) የህወሓት ቡድን የትግራይ ወጣቶችን እኔ ከሌለሁ መኖር አትችሉም እያለ የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው ሲሰራ መቆየቱን በቁጥጥር ስር የዋሉ የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት ተናገሩ።

የአገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል የመሸገውን ፅንፈኛ የህወሓት ጁንታ ለህግ ለማቅረብ እየወሰደ ያለው አርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

እስካሁን በተወሰዱ እርምጃዎች በርካታ አካባቢዎችን ከጁንታው ታጣቂ ኃይል ነፃ በማውጣት ለጦርነት ያሰለፋቸው የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚኒሻ አባላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ ይገኛሉ።

ባገኙት አጋጣሚም እጃቸውን ለአገር መከላከያ ሠራዊት በሰላም የሚሰጡም በርካቶች ናቸው።

በህግ ማስከበር ሂደቱ ከሽራሮ አካባቢ በቁጥጥር ስር ከዋሉት የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል አባላት መካከል አንዳንዶቹ እንደገለጹት ህወሓት የትግራይ ህዝብና ወጣቶችን "እኔ ከሌለሁ መኖር አትችሉም" በሚል የተሳሳተ ሀሳብ ሲያደናግር ቆይቷል።

በተለይ ወጣቶች ከልጅነታቸው ጀምሮ የተሳሳተ አመለካከት ይዘው እንዲያድጉ ለማድረግ "ህወሓት ከወደቀ መኖር ስለማትችሉ ለማንኛውም ትግል ተዘጋጁ" ሲል ለበርካታ ዓመታት መኖሩንም አመልክተዋል።

"በትግል ሂደት ደግሞ ያለእናንተ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊያሸንፍ የሚችል ኃይል በፍፁም የለም፣ አይኖርምም" በማለት ሲሰብክ ኖሯል ብለዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ በርካታ የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት ለአገር መከላከያ ሠራዊት እጃቸውን በሰላም የመስጠት ፍላጎት ስላላቸው አጋጣሚውን ነው የሚጠብቁትም ሲሉ ተናግረዋል።

ለዚህም አሁን ባለው ሁኔታ ለልዩ ኃይሉ አባላት ለአንድ ሰው የሚሰጠው "በቀን ሁለት ብስኩት ብቻ በመሆኑ ርሃብ እየተፈታተነውና እየተዳከመ መሆኑን በቁጥጥር ስር የዋሉት አባላት ገልጸዋል።

እነሱን ተዋጉ ብለው ካሰለፉ በኋላ አመራሮች የት እንዳሉ ሳይነግሯቸው እንደሚጠፉም ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የገለጹት።

በትግራይ ክልል ከህወሃት ትእዛዝ የሚያፈገፍግ ወጣት ወይም ነዋሪ ካጋጠመ የሚወሰድበት እርምጃ ከባድ እንደሆነም ተናግረዋል።

የህወሓት የጥፋት ቡድን ታዳጊ የትግራይ ወጣቶችን ከቤተሰቦቻቸው በመነጠል በሚያደርገው አፈና እና የጥፋት ተልዕኮ በርካታ ወላጆች ሃዘን እንደገባቸውም የልዩ ኃይል አባላቱ አስረድተዋል።

የትግራይ ወጣቶች በህወሓት የተሰበኩትን የተሳሳተ ትርክትና የስነ ልቦና ጭንቀት ለማስተካከል መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር እርምጃ በማጠናከር ህዝቡን በፍጥነት ነፃ እንዲያወጣውና ወጣቶችንም ከእልቂት እንዲታደግ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም