የኢትዮጵያ መንግሥት የከሀዲውን የሕወሓት መሪዎች ሕግ ፊት እንዲያቀርብ በውጭ የሚኖሩ 7 የሲቪክ ማህበራት ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንግሥት የከሀዲውን የሕወሓት መሪዎች ሕግ ፊት እንዲያቀርብ በውጭ የሚኖሩ 7 የሲቪክ ማህበራት ጠየቁ
ህዳር 6/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግሥት የከሀዲውን የሕወሓት መሪዎች ሕግ ፊት እንዲያቀርብ በአውሮፓና አሜሪካ የሚገኙ 7 የሲቪክ ማህበራት ጠይቀዋል።
ተቀማጭነታቸው በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ ያደረጉ ሰባት የኢትዮጵያ ሲቪክ ድርጅቶች በጋራ ባሰራጩት ባለ ሶስት ገፅ ደብዳቤ መንግስት የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ትክክለኛውን ግንዛቤ እንዲጨብጥና ድጋፍ እንዲያደርግ የሲቪክ ማህበራቱ የሚመለከታቸውን አካላት በዴብዳቤው ጠይቀዋል።
ደብዳቤው ለተባበሩት መንግሥታት፣ ለአፍሪካ ኅብረት፣ ለዓለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማትና ለልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲደረስ መደረጉም ተገልጿል።
የጽንፈኛው ሕወሓት ቡድን ሰሞኑን የዓለም አቀፍ የፕሮፓጋንዳ ማሽነሪ፣ ሌሎች ጽንፈኛ ኃይሎች እንዲሁም ባዕዳን ጋዜጠኞች እና ምሁራን ጋር በማበር በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚዲያዎች፣ በፓርላማ አባላት፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚደረግ የተቀነባበረ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑም ተጠቅሷል።
ድርጅቶቹ ያዘጋጁት ደብዳቤም በኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለውን፣ ግጭቱ መቼ፣ ለምን፣ ከምን ተነሥቶ ለሚሉ ጉዳዮችን በሚመለከት በርካታ የሐሰት ትርክቶች ከማሰራጨትም አልፎ "የእርስ በእርስ ጦርነት" እንደሆነ፣ መንግሥት ተገድዶ መግባቱ እውነት ሆኖ ሳለ "ትግራይን ለመውረር" እንደሚደረግ ለማቅረብ የተሄደበትን ውዥንብሮች እና ውሸቶችን ርቀት ለማጥራት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ኢትዮጵያውያን የሚገኙባቸው ሀገራት መንግሥታት፣ ለጋዜጠኞች፣ ለፓርላማ አባላት፣ ለሲቪክ ተቋማት በተለይም ጽንፈኞቹ እና የሕወሓት አሸባሪዎች የውጭ ተባባሪዎች ትኩረት ያደረጉባቸው እና የተሳሳተ ግንዛቤ ያላቸውን፣ የተሳሳተ መግለጫ ላወጡ ልዩ፣ ልዩ የመንግሥት እና ከመንግሥት ውጭ የሚገኙ ተፅዕኖ ፈጣሪ አካላት እንዲሁም ለሚዲያዎች፣ ጋዜጠኞች በማድረስ እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።