ቀጥታ፡

ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን የተከዜ ግድብ ተደብድቧል ሲል ያሰራጨው መረጃ ሀሰት ነው--የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል

አዲስ አበባ ህዳር 6/2013 (ኢዜአ) ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን "የተከዜ ኃይል ማመንጫ ግድብ በጦር ጄት ተደብድቧል" ሲል ያሰራጨው መረጃ ሀሰት መሆኑን የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የጽንፈኛው የህወሓት ቡድን መሪ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በቅርቡ በሰጡት መግለጫ "የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተከዜ ኃይል ማመንጫ ግድብን ደብድቧል" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ ጽንፈኛው ቡድን ግድቡን በሚመለከት የተሳሳተ መረጃ እያሰራጨ ይገኛል።

የቡድኑ ታጣቂዎች ከቀናቶች በፊት ግድቡን በኃይል ለመቆጣጠር በማለም በጥበቃ ሥራ በተሰማሩ የፌዴራል ፖሊስ አባላቶች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን አስታውሰዋል።

"ጥቃቱን ለመፈጸም በከፈቱት ተኩስ በግድቡ የኃይል ማስተላለፊያ ስዊች ላይ ጉዳት አድርሰዋል" ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅትም የቡድኑ አፈ-ቃላጤዎች የኃይል ማመንጫ ግድቡ በኢትዮጵያ የጦር ጄት እንደተደበደበ አድርገው የሀሰት መረጃ እያሰራጩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የጽንፈኛ ቡድኑ ታጣቂዎች የኃይል ማስተላለፊያ 'ስዊች' ላይ ካደረሱት ጥቃት ውጪ በግድቡ ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱን አብራርተዋል።

ግድቡ የያዘው 9 ነጥብ 3 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሊትር ውሃ መደበኛ ፍሰቱን ጠብቆ ወደታችኛው ተፋሰስ እየወረደ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ "ይህም ቡድኑ ስለግድቡ ያሰራጨው መረጃ ሀሰት ስለመሆኑ ማሳያ ነው" ብለዋል።

ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ይህን የሀሰት መረጃ የሚያሰራጨው ግድቡ በግንባታ ላይ እያለ የተነሱ ፎቶዎችን በመጠቀም መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ ጽንፈኛ ቡድኑ በየጊዜው የሚያሰራጫቸው የሀሰት መረጃዎችና ህገ-ወጥ ድርጊቶችን በትክከል እየተረዳ በመሆኑ የጥፋት ቡድኑ ተስፋ ወደመቁረጥ እየተሸጋገረ መሆኑንም አመልክተዋል።

ከዚህ አንጻር ቡድኑ ስለ ተከዜ ግድብ በተደጋጋሚ የሀሰት መረጃ ማሰራጨቱ ምናልባትም በግድቡ ላይ የተሰፋ መቁረጥ ጥቃት ለመሞከር ዕቅድ እንዳለው እንደሚያመላክት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ቡድኑ ከግድቡ ኃይል ማስተላለፊያ ስቴሽን ገመድ በመቀጠል የኤሌክትሪክ ኃይል እየተጠቀመ እንደሚገኝ መግለጹን ጠቅሰው፣ ድርጊቱ ወንጀል መሆኑን ተናግረዋል።

"ድርጊቱ ቡድኑ ምን ያህል ህገ-ወጥ መሆኑን በግልጽ ያሳያል" ብለዋል።

የተከዜ ኃይል ማመንጫ ግድብ 175 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን 300 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጭት አቅም አለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም