የአርባምንጭና የድሬዳዋ ነዋሪዎች የህወሃት ቡድን የፈጸመውን የሀገር ክህደት በሰልፍ አወገዙ - ኢዜአ አማርኛ
የአርባምንጭና የድሬዳዋ ነዋሪዎች የህወሃት ቡድን የፈጸመውን የሀገር ክህደት በሰልፍ አወገዙ
አርባ ምንጭ ፡ ድሬዳዋ ህዳር 6/2013 (ኢዜአ) የህወሃት ጁንታው ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የሚያወግዝና መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር ስራ የሚደግፍ ሰልፍ በአርባ ምንጭና በድሬዳዋ ከተሞች ተካሄደ፡፡
በአርባምጭ ከተማ በተካሄደው ሰልፍ የጋሞ ህዝብ 50 ሰንጋዎችና በጥሬ ገንዘብ 2 ሚሊዮን ብር ለሀገር መከላከያ ሰራሰዊት በድጋፍ አበርክቷል።
የከተማው ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ጫኮ በሰጡት አስተያየት ህወሃት ጽንፈኛው ቡድን በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሀገራችንን ለመበታተንና ለውጭ ጠላት አሳልፎ ለመስጠት የታለመ ነው።
"የጁንታው ቡድን ሲያለያየን ፣ሲከፋፍለንና ዘረኛ ሲያደርገን ቆይታል" ብለዋል።
መንግስት እያደረገ ላለው ህግ የማስከበር ስራ አቅም በፈቀደ ሁሉ ለመደገፍና እስከ ህይወት መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ወጣት ኤሊያስ ዓለሙ በበኩሉ "የህወሃት ቡድን የትግራይን ህዝብ ፀጥታን ከማስከበር ጎን ለጎን አንበጣ ሲከላከል በነበረ ሠራዊት ላይ ጥቃት ያደረሰ የእናት ጡት ነካሽ ነው" ብሏል፡፡
መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ከዳር ማድረስ እንደሚጠበቅበት ጠቁሞ ዘመቻውን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል ።
የትግራይ ህዝብም የማይበጀውን ጽንፈኛ ኃይል ለመንግስት አሳልፎ በመስጠት የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቋል፡፡
"የመከላከያ ሠራዊታችን የትግራይ ህዝብን ጸጥታ በመጠበቅና በግብርና በማገዝ ባለውለታው ነበር" ያሉት ደገሞ ወይዘሮ ጥሩነሽ ተስፋዬ ናቸው።
ጽንፈኛው ቡድን በአሁኑ ሰዓት የድርድር ጥያቄ የሚያቀርበው የማታለያና የራሱን አቅም ለማጠናከር በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚቀበለው አይደለም" ብለዋል።
የጋሞ ዞን አስተዳደር አቶ ብርሃኑ ዘውዴ "የህወሃት ቡድን በምንኮራበት የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም የሀገር ክህደቱን በግልጽ አሳይቷል" ብለዋል።
ቡድኑን ለመጨረሻ ጊዜ ለማሶገድ በሚደረገው ህግ የማስከበር ተግባር የጋሞ ህዝብ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል ።
በተመሳሳይ የድሬዳዋ ነዋሪዎች የህውሃት ጁንታ በሰሜን የመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመውን የሀገር ክህደት ወንጀል በሰልፍ አውግዘዋል።
ቡድኑ ለህግ መቅረብ እንደሚገባው ጠይቀዋል።
ነዋሪዎቹ የሀገር አለኝታና መከታ የሆነው ሰራዊት ለሚፈጽማቸው ሀገር የማዳንና ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረብ ዘመቻ ከጎኑ ቆመው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ በመፈክራቸው አስተጋብተዋል፡፡
"የድርድር ጊዜ አብቅቷል፤ ከሀገር አፍራሽ ጋር አንደራደርም" የሚሉ መፈክሮችን በማንገብ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል ።
የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ዘውድነሽ ነጋሽ በወቅቱ እንደገለጹት የህወሃት ቡድኖች ለ21 ዓመት በወንድምነት አብሯቸው ክፉ ደጉን ባሳለፈው የመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀሙት ግፍ በታሪክ መቼም ይቅር የማይባል ተግባር ነው፡፡
"የህወሃት ቡድኖች በፈጸሙት የዘር ማጥፋትና የጦር ወንጀል በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ቀርበው ሊቀጡ ይገባል" ያሉት ደግሞ አባ ዳሞታ መሐመድ ናቸው።
ሼህ መሐመድ አደም የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው የህወሃት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው ወንጀል በሰማይም በምድርም የተወገዘ ተግባር ነው" ሲሉ አውግዘዋል ።
ህወሃት ለህግ ለማቅረብ የተጀመረው ዘመቻ እንዲሳካ በገንዘብ ፣በጉልበትና በሌላም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መብራቴ ገብረየስ ህዝቡ ለመከላከያ ሠራዊት እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚመሰገንና የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ነዋሪው ለሠራዊቱ ደም በመለገስ ፣ በገንዘብና በቁስ እያበረከተ የሚገኘው ድጋፍ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ በበኩላቸው "ህዝቡ ለሠራዊቱ እያደረገ ስላለው ድጋፍ አመስግነዋል።
ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ የተጀመረው ዘመቻ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ህዝቡና አስተዳደሩ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።