የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) አመራርና አባላቶች ደም ለገሱ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) አመራርና አባላቶች ደም ለገሱ
አዲስ አበባ ህዳር 6/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) አመራርና አባላቶች “ደሜን ለሀገሬ” በሚል መሪ ቃል ደም ለግስዋል።
የፓርቲው አመራርና አባላቶች “ደሜን ለሀገሬ” በሚል መሪ ቃል ዛሬ በብሔራዊ ደም ባንክ በመገኘት ደም እየለገሱ ይገኛሉ።
በደም ልገሳ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ የደም ልገሳ መርሃ ግብሩ እየተከናወነ ያለው በሰሜን ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ለማስፈን ሕይወቱን እየሰጠ ላለው የአገር መከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች የጸጥታ አካላትን ለመደገፍ በሚል ነው።
በደም ልገሳው መርሃ ግብሩ በተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ የፓርቲው ቅርንጫፎች ያሉ አባላትም በመሳተፍ ላይ እንደሆኑ አቶ የሺዋስ ተናግረዋል።
መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር በህወሓት የጥፋት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ያደነቁት የፓርቲው ሊቀመንበር፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
ከአገር መከላከያ ጎን ለመሆን በደም ልገሳ መርሃ ግብር የተሳተፉት የፓርቲው አባላቶች ደም በመለገሳቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው በቀጣይም መከላከያ ሠራዊቱን ለማገዝ ተጨማሪ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ህዝቡ ለሠራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ በማስቀጠል ከመከላከያ ጎን መቆም እንዳለበትም ነው አባላቱ የተናገሩት።
መንግስት በሰሜን የአገርቱ ክፍል እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር ተግባር በመደገፍ በመላው አገሪቱ የድጋፍ መርሃ ግብር እየተከናወነ ይገኛል።